ምሳሌ 25 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 እነኚህም የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ሰዎች የገለበጧቸው የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው። 2 የእግዚአብሔር ክብር በምሥጥራዊ መንገድ ነገርን ማከናወን ነው፥ የነገሥታት ክብር ግን ነገርን መመርመር ነው። 3 እንደ ሰማይ ከፍታ እንደ ምድርም ጥልቀት የነገሥታት ልብ አይመረመርም። 4 ከብር ዝገትን አስወግድ፥ ፈጽሞም ይጠራል። 5 ከንጉሥ ፊት ክፉ ሰዎችን አርቅ፥ ዙፋኑም በጽድቅ ትጸናለች። 6 በንጉሥ ፊት አትመካ፥ በታላላቆችም ስፍራ አትቁም፥ 7 ዐይኖችህ ባዩት በመኰንን ፊት ከምትዋረድ፦ “ወደዚህ ከፍ በል” ብትባል ይሻልሃልና። 8 ባልንጀራህ ባሳፈረህ ጊዜ ኋላ እንዳትጸጸት ለሙግት ወደ ሽንጎ ፈጥነህ አትውጣ፥ 9 ሙግትህን ከባልንጀራህ ጋር በቀጥታ ፈጽም፥ የሌላ ሰው ምሥጢር ግን አትግለጥ፥ 10 የሚሰማ እንዳይነቅፍህ፥ ስምህንም ለሁልጊዜ እንዳያጠፋው፤ 11 በአግባብ የተነገረ ቃል፥ በብር ፃሕል ላይ እንደተቀመጠ ወርቅ ነው። 12 የሚሰማን ጆሮ የሚገሥጽ ጠቢባዊ ምክር፥ እንደ ወርቅ ጉትቻ እንደሚያንጸባርቅም ዕንቁ ነው። 13 ለላኩት የታመነ መልእክተኛ፥ በመከር ወራት ደስ እንዲሚያሰኝ የውርጭ ጠል ነው፥ የጌታውን ነፍስ ያሳርፋልና። 14 ስለ ስጦታው በሐሰት የሚመካ ሰው ዝናብ እንደሌለው ደመናና ነፋስ ነው። 15 በትዕግሥት አለቃ ይለዝባል፥ ገር ምላስ አጥንትን ይሰብራል። 16 በጣም እንዳትጠግብና እንዳትተፋው፥ ማር ባገኘህ ጊዜ የሚበቃህን ብላ። 17 እንዳይሰለቸውና እንዳይጠላህ፥ አዘውትረህ ወደ ባልንጀራህ ቤት አትሂድ። 18 በባልንጀራው ላይ በሐሰት የሚመሰክር እንደ መዶሻና እንደ ሰይፍ እንደ ተሳለም ቀስት ነው። 19 ከሃዲን ሰው በመከራ ጊዜ መተማመን እንደ ተሰበረ ጥርስና እንደ ሰለለ እግር ነው። 20 ባዘነ ሰው ላይ የሚዘምር፥ በብርድ ቀን ልብስን እንደሚገፍና በቁስልም ላይ ሆምጣጤ እንደሚጨምር ሰው ነው። 21 ጠላትህ ቢራብ እንጀራ አብላው፥ ቢጠማም ውኃ አጠጣው፥ 22 በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና፥ ጌታም ይሸልምሃልና። 23 የሰሜን ነፋስ ዝናብ ያመጣል፥ ሐሜተኛ ምላስም የሰውን ፊት ያስቈጣል። 24 ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ከመቀመጥ በሰገነት ማዕዘን ላይ መቀመጥ ይሻላል። 25 የቀዘቀዘ ውኃ ለደረቀ ጉሮሮ ደስ እንደሚያሰኝ፥ ከሩቅ አገር የመጣ መልካም ምሥራች እንዲሁ ነው። 26 በኀጥእ ፊት የሚወድቅ ጻድቅ እንደደፈረሰ ምንጭና እንደ ተበከለ ኩሬ ነው። 27 ብዙ ማር መብላት መልካም አይደለም፥ ክቡር ነገሮችን መፈለግ ግን የሚያስከብር ነው። 28 ራሱን መቆጣጠር የማይችል ሰው፥ ቅጥር እንደሌለው እንደ ፈረሰ ከተማ ነው። |