ምሳሌ 22 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 መልካም ስም ከብዙ ሃብት ይሻላል፥ መልካም ሞገስም ከብርና ከወርቅ ይበልጣል። 2 ሀብታምና ድሀ ይገናኛሉ፥ ሁለቱንም የፈጠራቸው ጌታ ነው። 3 ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፥ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይሄዱና ይጐዳሉ። 4 የትሕትናና ጌታን የመፍራት ውጤት ሀብት፥ ክብርና ሕይወት ናቸው። 5 እሾህና ወጥመድ በጠማማ ሰው መንገድ ላይ ይገኛሉ፥ ነፍሱን ግን የሚጠብቅ ከእነርሱ ይርቃል። 6 ልጅን ሊሄድ በሚገባው መንገድ ምራው፥ በሸመገለም ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም። 7 ሀብታም ድሆችን ይገዛል፥ ተበዳሪም የአበዳሪ ጥገኛ ነው። 8 ክፋትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል፥ የቁጣውም በትር ይጠፋል። 9 ርኅሩህ የተባረከ ይሆናል፥ ከእንጀራው ለድሀ ሰጥቶአልና። 10 ፌዘኛን ብታስወጣ ክርክር ይቆማል፥ ጠብና ስድብም ያልቃል። 11 የልብን ንጽሕናን የሚወድና ንግግሩ ለዛ ያለው ሰው፥ ንጉሥ ወዳጁ ይሆናል። 12 የጌታ ዐይኖች እውቀትን ይጠብቃሉ፥ የአታላዩን ቃላት ግን ይገለብጣል። 13 ሰነፍ ሰው፦ “ውጪ አንበሳ አለ፤ ብወጣ፥ በመንገዱ ላይ እሞታለሁ” ይላል። 14 የአመንዝራ ሴት አፍ የጠለቀ ጉድጓድ ነው፥ ጌታ የተቈጣው በውስጡ ይወድቃል። 15 ቂልነት በልጅ ልብ ውስጥ ተተብትቧል፥ የተግሣጽ በትር ግን ነፃ ያደርገዋል። 16 ለራሱ ጥቅም ሲል ድሀን የሚጐዳ፥ ለሀብታም የሚሰጥ፥ እርሱ ወደ ድህነት ይወድቃል። 17 ጆሮህን አዘንብለህ የጠቢባንን ቃላት ስማ፥ ልብህንም ወደ እውቀቴ አድርግ፥ 18 እነርሱን በውስጥህ ብትጠብቅ፥ በከንፈሮችህም ላይ የተዘጋጁ ቢሆኑ፥ አስደሳች ነገር ይሆንልሃልና። 19 እምነትህ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ እነሆ እነርሱን ዛሬ አስታወቅሁህ። 20-21 የእውነትን ቃል እርግጥነት አስታውቅህ ዘንድ፥ ለሚጠይቅህም እውነትን ቃል መመለስ ይቻልህ ዘንድ፥ በምክርና በእውቀት ሠላሳ ምሳሌዎችን አልጻፍሁልህምን? 22 ድሀን አትግፈፈው ድሀ ነውና፥ ችግረኛውንም በበር አትጨቁነው፥ 23 ምክንያቱም ጌታ ለእነርሱ ይሟገታልና፥ የቀሙአቸውንም ሰዎች ሕይወት ይቀማልና። 24 ከቁጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፥ ከንዴተኛም ጋር አትሂድ፥ 25 መንገዱን ተምረህ፥ ለነፍስህም ወጥመድ እንዳታገኝህ። 26 የምር ቃል እንደሚገቡ፥ ለባለ ዕዳዎች እንደሚዋሱ አትሁን፥ 27 መክፈል ባትችል፥ ለምን የምትተኛበት አልጋ ይወሰድብሃል? 28 አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፋልስ። 29 በሥራው ብልህ ሰው ትመለከታለህን? በነገሥታት ፊት ያገለግላል፥ በተራ ሰዎችም ፊት ሊያገለግል አይቆምም። |