ምሳሌ 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፥ 2 ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ፥ የእውቀትንም ቃል ለማስተዋል፥ 3 የጥበብን ትምህርት ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንም ለመቀበል፥ 4 ብልሃትን ለአላዋቂዎች ለመስጠት ለወጣቶችም እውቀትንና ጥንቃቄን፥ 5 ጠቢብ እነዚህን በመስማት ዐዋቂነትን ይጨምራል፥ አስተዋይም መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል። 6 ምሳሌንና ምሥጢርን የጠቢባንን ቃልና ዕንቆቅልሸ ለማስተዋል። 7 የዕውቀት መጀመሪያ ጌታን መፍራት ነው፥ ሞኞች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ። 8 ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ የእናትህንም ሕግ አትተው፥ 9 ለራስህ የሞገስ ዘውድ ለአንገትህም ሐብል ይሆንልሃልና። 10 ልጄ ሆይ፥ ኃጢአተኞች ቢያባብሉህ እሺ አትበል። 11 ደምን ለማፍሰስ “ና እናድባ፥ ለንጹሕም ያለ ምክንያት ወጥመድን እንሸምቅበት” ቢሉ፥ 12 “በሙሉ ሕይወት እያሉ፥ ከነነፍሳቸው፥ እንደ ሲኦል ሆነን እንዋጣቸው፥ ወደ ጉድጓድ እንደሚወድቁም ይሁኑ፥ 13 መልካምና ውድ ሀብት ሁሉ እናገኛለን፥ ከምርኮውም ቤታችንን እንሞላለን፥ 14 ዕጣህን ከእኛ ጋር ጣል፥ ለሁላችንም አንድ ከረጢት ይሁን ቢሉ”፥ 15 ልጄ ሆይ፥ ከእነርሱ ጋር በመንገድ አትሂድ፥ ከጎዳናቸውም እግርህን አርቅ፥ 16 እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉና፥ ደም ለማፍሰስም ይፈጥናሉና። 17 ወጥመድ በወፎች ዐይን ፊት በከንቱ ይተከላልና። 18 እነርሱም በደማቸው ላይ ያደባሉ፥ በነፍሳቸውም ላይ ይሸምቃሉ። 19 በግፍ ማትረፍ የሚፈልግ ሁሉ መንገዱ እንዲሁ ነው። የግፉ ባለቤትም ነፍስ ይነጠቃል። 20 ጥበብ በጎዳና ትጮኻለች፥ በአደባባይ ድምፅዋን ከፍ ታደርጋለች፥ 21 ግርግር ባለበት አደባባይ ትጣራለች፥ በከተማይቱ መግቢያ በር ቃልን ትናገራለች፦ 22 “እናንት አላዋቂዎች፥ እስከ መቼ አላዋቂነት ትወድዳላችሁ? ፌዘኞችም ፌዝን ይፈቅዳሉ? ሞኞችም እውቀትን ይጠላሉ? 23 ወደ ዘለፋዬ ተመለሱ፥ እነሆ፥ መንፈሴን አፈስስላችኋለሁ፥ ቃሌን አስተምራችኋለሁ። 24 በጠራሁ ጊዜ እምቢ ስላላችሁ፥ እጄን በዘረጋሁ ጊዜ ማንም ስላላስተዋለ፥ 25 ምክሬን ሁሉ ግን ችላ ስላላችሁ፥ ዘለፋዬንም ስላልተቀበላችሁ፥ 26 እኔም በእናንተ መጥፋት እስቃለሁ፥ ሽብር በመጣባችሁ ጊዜ አላግጥባችኋለሁ 27 ድንጋጤ እንደ ጐርፍ በደረሰባችሁ ጊዜ፥ ጥፋታችሁም እንደ ዐውሎ ነፋስ በመጣ ጊዜ፥ ጭንቅና መከራ በወረደባችሁ ጊዜ። 28 የዚያን ጊዜ ይጠሩኛል፥ እኔ ግን አልመልስም፥ ተግተው ይሹኛል፥ ነገር ግን አያገኙኝም። 29 እውቀትን ጠልተዋልና፥ ጌታንም መፍራት አልመረጡምና፥ 30 ምክሬን አልፈቀዱምና፥ ተግሣጼንም ሁሉ ንቀዋልና፥ 31 ስለዚህ የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ፥ የገዛ ራሳቸውን ምክር ይጠግባሉ። 32 አላዋቂዎችን ከጥበብ መራቅ ይገድላቸዋልና፥ ሞኞችንም ቸልተኛ መሆን ያጠፋቸዋልና። 33 የሚሰማኝ ግን ተረጋግቶ ይቀመጣል፥ ከክፉም ሥጋት ያርፋል።” |