Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘኍል 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የቀዓት ወገኖች

1 ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦

2 “ከሌዊ ልጆች መካከል የቀዓትን ልጆች በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች ላይ የሕዝብ ቈጠራ አድርግ፤

3 ዕድሜው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያለውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራን ለመሥራት ወደ አገልግሎት የሚገባውን ሁሉ ትቈጥራለህ።

4 በመገናኛው ድንኳን በንዋየ ቅድሳቱ ዘንድ የቀዓት ልጆች ሥራ ይህ ነው፤

5 ሰፈሩ ለመጓዝ በተነሣ ጊዜ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚሸፍነውን መጋረጃ ያውርዱ፥ የምስክሩንም ታቦት ይሸፍኑበት፤

6 በእርሱም ላይ የአስቆጣውን ቁርበት መሸፈኛ ያድርጉበት፥ ከእርሱም በላይ ሁለንተናው ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።

7 በተቀደሰው ኅብስቱ ገበታ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤ በእርሱም ላይ ወጭቶቹን፥ ሙዳዮችንም፥ ጽዋዎቹንም፥ ለመጠጥ ቁርባንም መንቀሎቹን ያስቀምጡበት፤ ሁልጊዜም የሚቀርበው እንጀራ በእርሱ ላይ ይሁን።

8 በእነርሱም ላይ ቀይ መጐናጸፊያ ይዘርጉ፥ በአስቆጣውም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።

9 ሰማያዊውንም መጐናጸፊያ ይውሰዱ፥ የመብራቱንም መቅረዝ፥ ቀንዲሎቹንም፥ መቆንጠጫዎቹንም፥ መተርኮሻዎቹንም፥ ዘይቱንም የሚያቀርቡባቸውን ዕቃዎች ሁሉ ይሸፍኑ፤

10 መቅረዙንና የመገልገያ ዕቃዎቹን ሁሉ በአቆስጣ ቁርበት መሸፈኛ ውስጥ ያኑሩት፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት።

11 በወርቁም መሠዊያ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።

12 በመቅደስም ውስጥ የሚገለገሉባቸውን የመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ይውሰዱ፥ በሰማያዊውም መጐናጸፊያ ውስጥ ያስቀምጡአቸው፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑአቸው፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉአቸው።

13 አመዱንም ከመሠዊያው ላይ ያስወግዱ፥ ሐምራዊውንም መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤

14 በእርሱም ላይ የሚገለገሉባቸውን የመሠውያውን ዕቃዎች ሁሉ፥ ጀሞዎቹን ሜንጦቹንም መጫሪያዎቹንም ጐድጓዳ ሳሕኖቹንም፥ የመሠዊያውን ዕቃ ሁሉ ያስቀምጡበት፤ በእርሱም ላይ የአቆስጣን ቁርበት መሸፈኛ ይዘርጉ፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ።

15 አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና የመቅደሱን ዕቃዎች ሁሉ መሸፈናቸውን በጨረሱ ጊዜ፥ ሰፈሩም ለመጓዝ ሲነሣ፥ የቀዓት ልጆች ሊሸከሙት ከዚያም በኋላ ይመጣሉ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅድሳቱን አይንኩ። የቀዓት ልጆች የሚሸከሙአቸው የመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች እነዚህ ናቸው።

16 “የካህኑም የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት መዓዛውም በሚያምር ዕጣን ላይ፥ ሁልጊዜም በሚቀርበው በእህሉ ቁርባንና በቅባቱ ዘይት ላይ ይሾም፤ ማደሪያውን ሁሉ፥ በእርሱም ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ መቅደሱንና ዕቃውን ይቆጣጠር።”

17 ጌታ ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦

18 “የቀዓትን ወገኖች ነገድ ከሌዋውያን መካከል አታጥፉአቸው፤

19 ነገር ግን እጅግ ቅዱስ ወደ ሆኑት ነገሮች በቀረቡ ጊዜ በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ እንዳይሞቱ እንዲህ አድርጉላቸው፦ አሮንና ልጆቹ ይግቡ፥ እያንዳንዱንም ሰው በየተግባሩና በየሥራው ጫና ይመድቡት፤

20 ነገር ግን እንዳይሞቱ ንዋየ ቅድሳቱን ለአንድ አፍታ እንኳ ለማየት አይግቡ።”


የጌድሶናውያን ወገኖች እና የሜራሪ ወገኖች

21 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

22 “እንዲሁም የጌድሶንን ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገኖቻቸውም የሕዝብ ቈጠራ አድርግ።

23 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራን ለመሥራት ወደ አገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ዕድሜአቸው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉትን ቁጠራቸው።

24 የጌድሶናውያን ወገኖች በማገልገልና በመሸከም የሚሰጡት አገልግሎት ይህ ነው፦

25 የማደሪያውን መጋረጆች፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መደረቢያውን፥ በእርሱም ላይ ያለውን የአቆስጣውን ቁርበት መሸፈኛ፥ የመገናኛውንም ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥

26 የአደባባዩንም መጋረጆች፥ በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለውን የአደባባዩን ደጃፍ መግብያ መጋረጃ፥ አውታሮቻቸውንም፥ የሚገለገሉባቸውንም ዕቃዎች ሁሉ ይሸከማሉ፤ እነርሱንም በሚመለከት ሊደረግ የሚገባውን ነገር ሁሉ ያድርጋሉ።

27 የጌድሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፥ ሸክማቸውም ሁሉ፥ ሥራቸውም ሁሉ በአሮንና በልጆቹ ትእዛዝ ይሁን፤ በየአገልግሎታቸውም የሚደርስባቸውን ሸክም ሁሉ ለእያንዳንዳቸው ትደለድላላችሁ።

28 የጌድሶናውያን ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ይህ ነው፤ ሥራቸውንም የካህኑ የአሮን ልጅ ኢታማር ይቈጣጠራል።

29 “የሜራሪንም ልጆች በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቁጠራቸው።

30 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራን ለመሥራት ወደ አገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ዕድሜአቸው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉትን ቁጠራቸው።

31 በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ባለው አገልግሎታቸው ሁሉ የሚሸከሙት፥ የማደሪያውን ሳንቆች፥ መቀርቀሪያዎቹንም፥ ምሶሶዎቹንም፥ እግሮቹንም፥

32 በዙሪያውም የሚቆሙትን የአደባባዩ ምሰሶች፥ እግሮቻቸውንም፥ ካስማዎቻቸውንም፥ አውታሮቻቸውንም፥ ዕቃዎቻቸውንና በተጓዳኝ የሚደረጉላቸውን አገልግሎቶች ሁሉ ነው፤ መሸከምም ያለባቸውን ዕቃዎች በየስሙ ትደለድላላችሁ።

33 በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር ቁጥጥር ሥር ሆነው በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ባለው አገልግሎታቸው ሁሉ የሜራሪ ልጆች ወገኖች አገልግሎት ይህ ነው።”


በሌዋውያን ላይ የተደረገ የሕዝብ ቈጠራ

34 ሙሴና አሮንም የሕቡም አለቆች የቀዓትን ልጆች በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቈጠሩአቸው።

35 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራን ለመሥራት ወደ አገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ዕድሜአቸው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉትን ቈጠሩአቸው፤

36 በየወገኖቻቸውም ከእነርሱ የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ኀምሳ ነበሩ።

37 ጌታ በሙሴ አንደበት እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከቀዓታውያን ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው።

38 በየወገኖቻቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት የጌድሶን ልጆች፥

39 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራን ለመሥራት ወደ አገልግሎት የገቡት፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥

40 በየወገኖቻቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሳ ነበሩ።

41 ጌታ በሙሴ አንደበት እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከጌድሶን ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው።

42 በየወገኖቻቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥

43 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራን ለመሥራት ወደ አገልግሎት የገቡት ሁሉ ዕድሜአቸው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥

44 በየወገኖቻቸው የተቈጠሩት ሦስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።

45 ጌታ በሙሴ አንደበት እንዳዘዘ፥ ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው።

46 በየወገኖቻቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች ከሌዋውያን የተቈጠሩት ሁሉ፥ ሙሴና አሮን የእስራኤልም አለቆች የቈጠሩአቸው፥

47 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራውን ለመሥራትና ዕቃውን ለመሸከም የገቡት ሁሉ፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥

48 ከእነርሱ የተቈጠሩት ስምንት ሺህ አምስት መቶ ሰማንያ ነበሩ።

49 እንደ ጌታ ትእዛዝ እያንዳንዳቸው በየአገልግሎታቸውና በየሸክማቸው በሙሴ ተደለደሉ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በእርሱ ተቈጠሩ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች