Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘኍል 29 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


መለከቶች የሚነፉበት የበዓል ቁርባን

1 በሰባተኛውም ወር ከወሩ በመጀመሪያ ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፤ መለከቶች የሚነፉበት ቀን ነው።

2 ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤

3 እንዲሁም ደግሞ ለእህል ቁርባናቸው በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለወይፈኑ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራው በግ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥

4 ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ ታቀርባላችሁ።

5 ማስተስረያም እንዲሆንላችሁ አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ።

6 በወሩ መባቻ ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን፥ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን፥ ከመጠጡም ቁርባን ሌላ፥ እንደ ሕጋቸው ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርቡ ናቸው።


የማስተስረያ ቀን ቁርባን

7 በዚህም በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም አዋርዱ፤ ምንም ዓይነት ሥራ አትሥሩ።

8 ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ ነውር የሌለባቸውም ይሁኑ።

9 ለእህል ቁርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለወይፈኑ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአንድ አውራ በግ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥

10 ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ ታቀርባላችሁ፤

11 እንዲሁም ከሚያስተሰርየው ከኃጢአት መሥዋዕት፥ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን፥ ከመጠጥ ቁርባናቸውም ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።።


የዳስ በዓል ቁርባን

12 በሰባተኛውም ወር በዓሥራ አምስተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፥ ሰባት ቀንም ለጌታ በዓል አድርጋችሁ ታከብራላችሁ።

13 ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት፥ ዐሥራ ሦስት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ነውር የሌለባቸውም ይሁኑ።

14 ለእህል ቁርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለዐሥራ ሦስት ወይፈኖች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለሁለቱ አውራ በጎች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥

15 ለዐሥራ አራቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ ታቀርባላችሁ፤

16 ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።

17 በሁለተኛውም ቀን ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችን፥ ሁለት አውራ በጎችን፥ ነውር የሌለባቸው ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶችን፥

18 ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤

19 ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባናቸው ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።

20 “በሦስተኛውም ቀን ዐሥራ አንድ ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥

21 ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤

22 ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።

23 በአራተኛውም ቀን ዐሥር ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥

24 ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸውም መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤

25 ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።

26 “በአምስተኛውም ቀን ዘጠኝ ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥

27 ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤

28 ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።

29 “በስድስተኛውም ቀን ስምንት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥

30 ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤

31 ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።

32 “በሰባተኛውም ቀን ሰባት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥

33 ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤

34 ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።

35 “በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ፤ የጉልበት ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።

36 ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥

37 ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቁርባናቸውንና የመጠጥ ቁርባናቸውን እንደ ቁጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ታቀርባላችሁ፤

38 ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን ከመጠጡም ቁርባን ሌላ ለኃጢአት መሥዋዕት ደግሞ አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ።

39 “እነዚህንም፥ ከስእለታችሁና በፈቃዳችሁ ከምታመጡት ቁርባን ሌላ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለእህልም ለመጠጥም ቁርባን፥ ለአንድነትም መሥዋዕታችሁ በበዓላችሁ ጊዜ ለጌታ አቅርቡ።

40 ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ጌታ እርሱን ያዘዘውን ሁሉ ነገራቸው።”

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች