Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘኍል 19 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የቀይዋ ጊደር ሥርዓት

1 ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦

2 “ጌታ ያዘዘው የሕጉ ትእዛዝ ይህ ነው፤ መልካሚቱን፥ ነውርም የሌለባትን፥ ቀንበርም ያልተጫነባትን ቀይ ጊደር እንዲያመጡልህ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው።

3 እርሷንም ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጣላችሁ፥ እርሷም ከሰፈር ወደ ውጭ ትወሰዳለች፥ እርሷም በእርሱ ፊት ትታረዳለች።

4 ካህኑም አልዓዛር ከደምዋ በጣቱ ይወስዳል፥ ከደምዋም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል።

5 ጊደሪቱም በፊቱ ትቃጠላለች፤ ቁርበትዋም ሥጋዋም ደምዋም ፈርስዋም ይቃጠላል።

6 ካህኑም የዝግባ እንጨት ሂሶጵም ቀይ ግምጃም ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት መካከል ይጥለዋል።

7 ካህኑም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል፤ ካህኑም እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል።

8 ያቃጠላትም ሰው ልብሱን በውኃ ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።

9 ንጹሕም ሰው የጊደሪቱን አመድ ይሰበስባል ከሰፈሩም ውጭ በንጹሕ ስፍራ ያኖረዋል፤ ርኩሰትንም የሚያነጻ ውኃ ተደርጎ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ይጠበቃል፤ ከኃጢአት ለማንጻት የሚሆን ነው።

10 የጊደሪቱንም አመድ የሰበሰበው ሰው ልብሱን ያጥባል እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ለሚኖር መጻተኛ ለዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል።

11 “የሞተውን የማናቸውንም ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል፤

12 በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን በውኃ ያነጻል፥ በዚህም ንጹሕ ይሆናል፤ ነገር ግን በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ባያነጻ ንጹሕ አይሆንም።

13 የሞተውን ሰው በድን የነካ ማናቸውም ሰው ሁለመናውን ባያነጻ የጌታን ማደሪያ ያረክሳል፤ ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ በእርሱም ላይ ከርኩሰት የሚያነጻ ውኃ አልተረጨምና ርኩስ ይሆናል፤ ርኩሰቱ ገና በእርሱ ላይ ነው።

14 “ሰው በድንኳን ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባ ሁሉ በድንኳኑም ውስጥ ያለው ሁሉ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል።

15 መክደኛው ያልታሰረ የተከፈተ ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው።

16 በተንጣለለው ሜዳ በሰይፍ የተገደለውን ወይም የሞተውን በድን ወይም የሰውን ዐፅም ወይም መቃብር የሚነካ ማናቸውም ሰው ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል።

17 ከኃጢአት ለማንጻት እንድትሆን ከተቃጠለችው ጊደር አመድ ለረከሰው ሰው ይወስዱለታል፥ በዕቃውም ውስጥ የምንጭ ውኃ ይጨመርበታል።

18 ንጹሕም ሰው ሂሶጱን ወስዶ በውኃው ውስጥ ይነክረዋል፤ በድንኳኑም፥ በዕቃውም ሁሉ፥ በዚያም ባሉ ሰዎች ላይ፥ ዐፅሙንም ወይም የተገደለውን ወይም የሞተውን ወይም መቃብሩን በነካው ሰው ላይ ይረጨዋል፤

19 ንጹሑም ሰው በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ርኩስ በሆነው ሰው ላይ ይረጨዋል፤ በሰባተኛውም ቀን ያነጻዋል፤ እርሱም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ በመሸም ጊዜ ንጹሕ ይሆናል።

20 “ሰውም ርኩስ ቢሆን ሁለመናውንም ባያነጻ፥ ያ ሰው የጌታን መቅደስ አርክሶአልና ከጉባኤው መካከል ተለይቶ ይጠፋል፤ ከርኩሰት የሚያነጻውን ውኃ አልተረጨም፤ ርኩስ ነው።

21 ይህም ለእነርሱ የዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል፤ ከርኩሰት የሚያነጻውን ውኃ የሚረጨው ሰው ልብሱን ያጥባል፤ ከርኩሰትም የሚያነጻውን ውኃ የሚነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

22 የረከሰውም ሰው የሚነካው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።”

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች