ዘኍል 17 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የአሮን በትር ማቈጥቈጡ 1 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “ለእስራኤል ልጆች ተናገር፥ ከእነርሱም ከእያንዳንዱ ከየአባቶቻቸው ቤት አንድ አንድ በትር፥ ከአለቆቻቸው ሁሉ ከየአባቶቻቸው ቤት ዐሥራ ሁለት በትሮች፥ ውሰድ፤ የእያንዳንዱንም ስም በየበትሩ ላይ ጻፍ። 3 በሌዊም በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍ። ለእያንዳንዱ ለአባቶቻቸው ቤት አለቃ አንድ በትር ይኖራቸዋልና። 4 እኔ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት ለፊት አኑራቸው። 5 እንዲህም ይሆናል፤ የመረጥሁት ሰው በትር ታቈጠቁጣለች፥ በእናንተም ላይ ያጉረመረሙትን የእስራኤልን ልጆች ማጉረምረም ከእኔ ዘንድ አጠፋለሁ።” 6 ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ አለቆቻቸው ሁሉ ዐሥራ ሁለት በትሮች፥ እያንዳንዱም አለቃ በየአባቱ ቤት አንድ አንድ በትር፥ ሰጡት፤ የአሮንም በትር በበትሮቻቸው መካከል ነበረች። 7 ሙሴም በትሮቹን በጌታ ፊት በምስክሩ ድንኳን ውስጥ አኖራቸው። 8 እንዲህም ሆነ፤ በማግስቱ ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገባ፤ እነሆም፥ ለሌዊ ቤት የሆነው የአሮን በትር አቈጥቁጦ፥ እምቡጥም አውጥቶ፥ አበባም አብቦ፥ የበሰለ ለውዝም አፍርቶ ነበር። 9 ሙሴም በትሮችን ሁሉ ከጌታ ፊት ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አወጣቸው፤ እነርሱም አዩ፥ እያንዳንዱም በትሩን ወሰደ። 10 ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የአሮንን በትር ወደ ምስክሩ ፊት መልሰህ አኑር፤ እርሱም ለሚያምፁብኝ ልጆች ምልክት ሆኖ ይቀመጥ፤ እነርሱም እንዳይሞቱ በእኔ ላይ ማጉረምረማቸውን ታስቆምበታለህ።” 11 ሙሴም እንዲሁ አደረገ፤ ጌታ እንዳዘዘው እንዲሁ እርሱ አደረገ። 12 የእስራኤልም ልጆች ሙሴን እንዲህ አሉት፦ “እነሆ፥ እንሞታለን፥ እንጠፋለን፥ ሁላችንም እንጠፋለን። 13 ፈጽሞ ወደ ጌታ ማደሪያ የሚቀርብ ሁሉ፥ ይሞታል፤ በውኑ ሁላችን እንሞታለንን?” |