Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘኍል 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የእስራኤል የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ

1 ጌታም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን፥ ከግብጽ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ዓመት እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

2 “የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እያንዳንዱን ወንድ አንድ በአንድ እንደየስማቸው ቍጥር የሕዝብ ቈጠራ አድርጉ።

3 ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለውን፥ ከእስራኤል ወደ ጦርነት የሚወጣውን ሁሉ፥ አንተና አሮን በየሠራዊቶቻቸው ቁጠሩአቸው።

4 ከየነገዱም አንድ ሰው የአባቶቹ ቤት አለቃ የሆነ ከእናንተ ጋር ይሁን።

5 ከእናንተም ጋር ሆነው የሚረዱዋችሁ ሰዎች ስሞቻቸው እነዚህ ናቸው፤ ከሮቤል የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር፥

6 ከስምዖን የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፥

7 ከይሁዳ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፥

8 ከይሳኮር የሶገር ልጅ ናትናኤል፥

9 ከዛብሎን የኬሎን ልጅ ኤልያብ፥

10 ከዮሴፍ ልጆች፥ ከኤፍሬም የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፥ ከምናሴ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል፥

11 ከብንያም የጋዴዮን ልጅ አቢዳን፥

12 ከዳን የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፥

13 ከአሴር የኤክራን ልጅ ፋግኤል፥

14 ከጋድ የደዑኤል ልጅ ኤሊሳፍ፥

15 ከንፍታሌም የዔናን ልጅ አሒራዕ።”

16 ከማኅበሩ የተመረጡ የእስራኤል የወገኖቻቸው አውራዎች፥ የአባቶቻቸው ነገድ አለቆች እነዚህ ነበሩ።

17 ሙሴና አሮንም እነዚህን በስማቸው ተጠርተው የነበሩትን ሰዎች ወሰዱአቸው፤

18 በሁለተኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ማኅበሩን ሁሉ ሰብሰቡአቸው፤ እነርሱም ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለውን አንድ በአንድ እንደየስማቸው ቍጥር፥ በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ትውልዳቸውን መዘገቡ።

19 ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ በሲና ምድረ በዳ ቈጠራቸው።

20 “የእስራኤል በኩር የሮቤል ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ አንድ በአንድ፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለውን ወንድ ሁሉ፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥

21 ከሮቤል ነገድ የተቈጠሩ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።

22 “የስምዖን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቍጥር፥ አንድ በአንድ የተቈጠሩት፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለውን ወንድ ሁሉ፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥

23 ከስምዖን ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ።

24 “የጋድ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥

25 ከጋድ ነገድ የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ኀምሳ ነበሩ።

26 “የይሁዳ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥

27 ከይሁዳ ነገድ የተቈጠሩት ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።

28 “የይሳኮር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥

29 ከይሳኮር ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።

30 “የዛብሎን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥

31 ከዛብሎን ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።

32 “ከዮሴፍ ልጆች፥ የኤፍሬም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥

33 ከኤፍሬም ነገድ የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።

34 “የምናሴ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥

35 ከምናሴ ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።

36 “የብንያም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥

37 ከብንያም ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።

38 “የዳን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥

39 ከዳን ነገድ የተቈጠሩት ስልሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።

40 “የአሴር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥

41 ከአሴር ነገድ የተቈጠሩት አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።

42 “የንፍታሌም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገኖቻቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥

43 ከንፍታሌም ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።

44 “እነዚህ ተቈጥረው የነበሩ ናቸው፤ እነርሱን ሙሴና አሮን ከእስራኤል አለቆች፥ ዐሥራ ሁለት ሰዎች፥ እያንዳንዳቸው የአባቶቻቸውን ቤቶች ይወክሉ ከነበሩ ጋር በመሆን ቈጠሩአቸው።

45 ከእስራኤልም ልጆች የተቈጠሩት ሁሉ፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለው፥ ከእስራኤል ወደ ጦርነት የሚወጣው ሁሉ፥

46 የተቈጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ኀምሳ ነበሩ።

47 “ሌዋውያን ግን በየአባቶቻቸው ነገድ ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም።

48 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

49 የሌዊን ነገድ ብቻ አትቁጠረው፥ የሕዝብ ቈጠራ ስታደርግ እነርሱን ከእስራኤል ልጆች ጋር አትቁጠር፤

50 ነገር ግን በምስክሩ ማደሪያና በዕቃው ሁሉ የእርሱም በሆነው ነገር ሁሉ ላይ ሌዋውያንን ሹማቸው። ማደሪያውንና ዕቃዎቹን ሁሉ ይሸከሙ፥ ያገልግሉትም፥ በማደሪያውም ዙሪያ ይስፈሩ።

51 ማደሪያውም ሲነሣ ሌዋውያን ይንቀሉት፤ ማደሪያውም በሚተከል ጊዜ ሌዋውያን ይትከሉት፤ ሌላ ሰው ግን ቢቀርብ ይገደል።

52 የእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ በየሰፈሩ፥ በየዓላማውም፥ በየጭፍራውም ይሰፍራሉ።

53 ነገር ግን በእስራኤል ልጆች ጉባኤ ላይ ቁጣ እንዳይወርድ ሌዋውያን በምስክሩ ማደሪያ ዙሪያ ይስፈሩ፤ ሌዋውያንም የምስክሩን ማደሪያ ይጠብቁ።”

54 የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረጉ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች