Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ነህምያ 5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ነህምያ ከጭቆና ጋር መጋፈጡ

1 የሕዝቡና የሚስቶቻቸው ጩኸት በወንድሞቻቸው በአይሁድ ላይ ትልቅ ሆነ።

2 እንዲህ የሚሉ ነበሩ፦ “እኛ፥ ወንዶች ልጆቻችንና ሴቶች ልጆቻችን ብዙ ነን፤ እንድንበላና በሕይወት እንድንኖር እህልን እንውሰድ”

3 እንዲህ የሚሉም ነበሩ፦ “በራቡ ጊዜ እህል እንድንወስድ እርሻችን፥ የወይን ቦታችንንና ቤታችንን አስይዘናል”

4 እንዲህ የሚሉ ደግሞ ነበሩ፦ “ለንጉሡ ግብር ለመክፈል እርሻችንንና የወይን ቦታችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል፤

5 አሁንም ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ፥ ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው፤ እነሆ ወንዶች ልጆቻችንና ሴቶች ልጆቻችን ባርያዎች እንዲሆኑ ለማምጣት ተገደናል፥ አንደንድ ሴቶች ልጆቻችን አሁንም ለባርነት ተወስደዋል፤ እርሻችንና የወይን ቦታችን ለሌሎች ስለሆነ ኃይል በእጃችን የለም።”

6 እኔም ጩኸታቸውንና እነዚህን ቃላት በሰማሁ ጊዜ እጅግ ተቆጣሁ።

7 በልቤም አሰብሁና መኳንንቶቹንና ሹማምቱን ተከራከርኋቸው፥ እንዲህም አልኋቸው፦ “እያንዳንዳችሁ ለወንድማችሁ በአራጣ ታበድራላችሁ”፤ ትልቅ ጉባኤም ሰበሰብሁባቸው።

8 እኔም እንዲህ አልኳቸው፦ “ለአሕዛብ የተሸጡትን አይሁድ ወንድሞቻችንን በተቻለን መጠን ተቤዠን፥ እናንተ ደግሞ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁ? እነርሱስ ለእኛ ይሸጣሉን? እነርሱም ዝም አሉ፥ የሚመልሱትንም ቃል አጡ።

9 እንዲህም አልኳቸው፦ የምታደርጉት ነገር መልካም አይደለም፤ ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት መሄድ አይገባችሁምን?

10 እኔ፥ ወንድሞቼና አገልጋዮቼ ገንዘብና እህል አበድረናቸዋል፤ ይህን አራጣ ግን እባካችሁ እንተወው።

11 በብድር የያዛችሁትን እርሻቸውን፥ የወይን ቦታቸውን፥ ወይራቸውን፥ ቤታቸውን፥ ከመቶ አንድ የወሰዳችሁትን ብር፥ እህሉን፥ አዲሱን ወይን ጠጅና ዘይት እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው።”

12 እነርሱም፦ “እንመልስላቸዋለን፥ ከእነርሱም ምንም አንፈልግም፤ አንተ እንዳልኸው እናደርጋለን” አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ ቃል እንደገቡት እንዲያደርጉ አስማልኳቸው።

13 ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና፦ “ይህን ቃል የማይፈጽመውን ሰው እግዚአብሔር ከቤቱና ከንብረቱ እንደዚሁ ያራግፈው፤ እንዲሁም የተራገፈና ባዶ ይሁን” አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ፦ “አሜን” አሉና ጌታን አመሰገኑ፤ ሕዝቡ ቃል ኪዳኑ አደረጉ።

14 በይሁዳ ምድር ላይ ገዢ እንድሆን ከተሾምሁበት፥ ከንጉሡ አርታሕሻስት ከሀያኛው ዓመት ጀምሮ እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ለዐሥራ ሁለት ዓመት ያህል እኔና ወንድሞቼ የንጉሡን ምግብ አልበላንም።

15 ከእኔ በፊት የነበሩት የቀድሞ ገዢዎች ግን በሕዝቡ ላይ አክብደውባቸው ነበር፥ ምግብ፥ ወይና አርባ ሰቅል ብር ከእነሱ ይወስዱ ነበር፤ አገልጋዮቻቸው ደግሞ ሕዝቡን ይጨቁኑአቸው ነበር፤ እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈራሁ እንዲህ አላደረግሁም።

16 በተጨማሪም ለዚህ የቅጥር ሥራ እራሴን ሰጠሁ፥ እርሻም አልገዛንም፤ አገልጋዮቼም ሁሉ ወደዚያው ወደ ሥራው ተሰበሰቡ።

17 በዙሪያችን ካሉት፥ ወደ እኛ ከመጡት አሕዛብ ሌላ ከአይሁድና ከሹማምቱ መቶ አምሳ ሰዎች በገበታዬ ነበሩ።

18 ለአንድ ቀን ይሠራ የነበረው አንድ በሬ፥ ስድስት የተመረጡ በጎች ነበር፤ ዶሮዎችም ይዘጋጁልኝ ነበር፥ በየዐሥር ቀኑም ብዛት ያለው ልዩ ልዩ ዓይነት ወይን ጠጅ ይዘጋጅልኝ ነበር፤ ይህም ሆኖ ግን የንጉሡን ምግብ አልሻም ነበር በዚህ ሕዝብ ላይ ሥራው ከብዶ ነበርና።

19 አምላኬ ሆይ፥ ለዚህ ሕዝብ ያድረግሁትን ሁሉ ለመልካምነት አስብልኝ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች