Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ሚክያስ 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


በሰማርያ ላይ የተላለፈ ፍርድ

1 በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታምና በአካዝ በሕዝቅያስም ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው፥ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው፥ የጌታ ቃል ይህ ነው።

2 ሕዝቦች ሆይ! ሁላችሁም ስሙ፤ ምድርና ሞላዋ ታድምጥ፤ ጌታ በቅዱስ መቅደሱ ሆኖ፥ ጌታ አምላክ በእናንተ ላይ ይመስክርባችሁ።

3 እነሆ፥ ጌታ ከስፍራው ይወጣልና፥ ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይራመዳል።

4 ተራሮች በሥሩ ይቀልጣሉ፥ ሸለቆዎችም በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፥ ከቁልቁለት እንደሚወርድ ውኃ፥ ይሰነጠቃሉ።

5 ይህ ሁሉ ስለ ያዕቆብ በደልና ስለ እስራኤል ቤት ኃጢአት ነው። የያዕቆብ በደል ምንድነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኮረብታው መስገጃ ምንድነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን?

6 ስለዚህ ሰማርያን በሜዳ እንደሚገኝ የድንጋይ ክምር፥ ወይን እንደሚተከልበት ስፍራ አደርጋታለሁ፤ ድንጋዮችዋን ወደ ሸለቆ አፈሰዋለሁ፥ መሠረቶችዋንም እገልጣለሁ።

7 የተቀረጹትም ምስሎችዋ ይደቅቃሉ፥ በግልሙትና ያገኘችው ዋጋ ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፥ ጣዖቶችዋንም ሁሉ አጠፋለሁ፤ በግልሙትና ዋጋ ሰብስባቸዋለችና፥ ወደ ግልሙትና ዋጋ ይመለሳሉ።


የይሁዳ ከተሞች ፍርድ

8 በዚህ ምክንያት አለቅሳለሁ፥ ዋይ ዋይ እላለሁ፥ ባዶ እግሬንና ራቁቴን እሄዳለሁ፤ እንደ ቀበሮ አላዝናለሁ፥ እንደ ሰጎን ልጆችም የዋይታ ድምፅ አሰማለሁ።

9 ቁስልዋ የማይፈወስ ነውና፤ ወደ ይሁዳ መጥቷል፥ ወደ ሕዝቤ በር ወደ ኢየሩሳሌምም ደርሶአል።

10 በጋት አታውሩት፥ በፍጹም አታልቅሱ፤ በቤትልዓፍራ በትቢያ ላይ ተንከባለሉ።

11 በሻፊር የምትቀመጪ ሆይ፥ በራቁትነትና በእፍረት እለፊ፤ በጻኣናን የምትቀመጠው አልወጣችም፤ የቤትሐኤጼል ለቅሶ የመቆሚያ ስፍራውን ከእናንተ ይወስዳል።

12 በማሮት የምትቀመጠው መልካም ነገርን ትጠባበቃለችና፤ ነገር ግን ክፉ ነገር ከጌታ እስከ ኢየሩሳሌም በር ድረስ ወርዶአል።

13 በላኪሽ የምትቀመጪ ሆይ፥ ሠረገላውን ከፈረሱ ጋር አያይዢ፤ እርሷ ለጽዮን ሴት ልጆች የኃጢአት መጀመሪያ ነበረች፤ የእስራኤል በደል በአንቺ ዘንድ ተገኝቶአልና።

14 ስለዚህ ለሞሬሼት ጋት የመሸኛ ስጦታዎችን ትሰጪአለሽ፤ የአክዚብ ቤቶች ለእስራኤል ነገሥታት መታለያ ይሆናሉ።

15 በማሬሻ የምትቀመጪ ሆይ፥ ወራሽ አመጣብሻለሁ፤ የእስራኤል ክብር ወደ ዓዱላም ይመጣል።

16 ደስ ስለምትሰኚባቸው ልጆች ራስሽን ንጪ፥ ፀጉርሽንም ተቆረጪ፤ መላጣነትሽን እንደ ንስር አስፊ፤ በምርኮ ከአንቺ ተወስደዋልና።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች