ማቴዎስ 28 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የኢየሱስ ከሙታን መነሣት ( ማር. 16፥1-8 ፤ ሉቃ. 24፥1-12 ፤ ዮሐ. 20፥1-10 ) 1 በሰንበት መጨረሻ ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሌላይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። 2 እነሆ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ መጥቶም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። 3 መልኩ እንደ መብረቅ፥ ልብሱ ደግሞ እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። 4 እርሱን ከመፍራት የተነሣ ጠባቂዎቹ ተንቀጠቀጡ፤ እንደ ሞተ ሰው ሆኑ። 5 መልአኩም ሴቶቹን እንዲህ አላቸው “አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁና፤ 6 በዚህ የለም፤ እንደ ተናገረው ተነሥቶአልና፤ ተኝቶ የነበረበትን ስፍራ ኑና እዩ። 7 ፈጥናችሁ ሂዱና ‘ከሙታን ተነሥቶአል፤ እነሆ ወደ ገሊላ ቀድሞአችሁ ይሄዳል፤ በዚያም ታዩታላችሁ’ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። እነሆ ነግሬአችኋለሁ።” 8 በፍርሃትና በታላቅ ደስታ ፈጥነው ከመቃብሩ ሄዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሊነግሩ ሮጡ። 9 እነሆ ኢየሱስ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። 10 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አትፍሩ፤ ሄዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩአቸው፤ በዚያም ያዩኛል” አላቸው። 11 ሲሄዱም ሳሉ እነሆ ከጠባቂዎቹ አንዳንዶቹ ወደ ከተማ መጥተው የሆነውን ሁሉ ለሊቃነ ካህናቱ አወሩ። 12 ከሽማግሌዎች ጋር ተሰብስበው ተማከሩና ለወታደሮቹ ብዙ ገንዘብ ሰጡአቸው፥ 13 እንዲህም አሉአቸው፦ “‘እኛ ተኝተን ሳለን ደቀመዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት’ በሉ። 14 ይህም በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደሆነ፥ እኛ እናሳምነዋለን፤ እናንተም ከሥጋት ነጻ እንድትሆኑ እናደርጋለን።” 15 እነርሱም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ አስተማሩአቸው አደረጉ። ይህም ነገር በአይሁድ ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ይወራል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲያስተምሩ እንዳዘዛቸው ( ማር. 16፥14-18 ፤ ሉቃ. 24፥36-49 ፤ ዮሐ. 20፥19-23 ፤ የሐዋ. 1፥6-8 ) 16 ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፤ 17 ባዩትም ጊዜ ሰገዱ፤ አንዳዶቹ ግን ተጠራጠሩ። 18 ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ አላቸው “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል። 19 ስለዚህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፥ በወልድና መንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ 20 ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሩአቸው፤ እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” |