ማቴዎስ 18 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው? ( ማር. 9፥33-37 ፤ ሉቃ. 9፥46-48 ) 1 በዚያች ሰዓት ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው? ብለው ጠየቁት። 2 ሕፃን ልጅ ጠርቶ በመካከላቸው አቆመው፤ 3 እንዲህም አለ “እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁና እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። 4 እንደዚህ ሕፃን ትሑት የሆነ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጠው እርሱ ነው። 5 “እንደዚህ ሕፃን ያለውን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ 6 በእኔ ከሚያምኑ ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰጥም ይሻለዋል። ስለሚመጣው መሰናክል ( ማር. 9፥42-48 ፤ ሉቃ. 17፥1-2 ) 7 “ከማሰናከያው የተነሣ ዓለም ወዮላት፤ ማሰናከያ ግድ ይመጣልና፤ የማሰናከያ ማምጫ ምክንያት የሆነው ያ ሰው ግን ወዮለት! 8 እጅህ ወይም እግርህ ካሰናከለህ ቆርጠህ ጣለው፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘለዓለም እሳት ከምትጣል፥ አንካሳ ወይም ጉንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። 9 ዓይንህ ካሰናከለህ አውጥተህ ጣለው፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል፥ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃል። 10 “ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና። 11 የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ለማዳን ነው። የጠፋው በግ ምሳሌ ( ሉቃ. 15፥3-7 ) 12 “ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩት ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ሊፈልግ አይሄድምን? 13 እውነት እላችኋለሁ፥ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሱ ደስ ይለዋል። 14 እንደዚሁም ደግሞ ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱ እንኳ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም። ወንድምን ስለመገሠጽ ( ሉቃ. 17፥3 ) 15 “ወንድምህ ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ገሥጸው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ታተርፈዋለህ፤ 16 ባይሰማህ ግን አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር ቃል ነገር ሁሉ ይጸናልና፥ 17 እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ቁጠረው። 18 እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈቱትም ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል። 19 ደግሞም እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር ላይ በሚለምኑት በማንኛውም ነገር ሁሉ ቢስማሙ፥ በሰማያት ባለው አባቴ ይደረግላቸዋል። 20 ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው አለሁና።” ይቅርታ ስለ ማድረግ 21 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ቀርቦ “ጌታ ሆይ! ወንድሜ ስንት ጊዜ ቢበድለኝ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” አለው። 22 ኢየሱስም እንዲህ አለው “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም። 23 “ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ከባርያዎቹ ጋር ሊተሳሰብ የፈለገን ንጉሥ ትመስላለች። 24 መተሳሰብ በጀመረ ጊዜ፥ አስር ሺህ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። 25 መክፈልም ሲያቅተው እርሱ፥ ሚስቱ፥ ልጆቹና ያለውም ሁሉ ተሽጠው ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። 26 ስለዚህ ባርያው ወድቆ ተንበረከከና ‘እባክህ ታገሠኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤’ አለው። 27 የዚያም ባርያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፤ ዕዳውንም ተወለት። 28 ነገር ግን ያ ባርያ ከዚያ ወጥቶ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን ከባልንጀሮቹ ባርያዎች አንዱን አገኘና ‘ዕዳህን ክፈለኝ’ ብሎ አንቆ ያዘው። 29 ያል ባልንጀራው ባርያ ወድቆ ‘እባክህ ታገሠኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤’ ብሎ ለመነው። 30 እርሱ ግን አልፈለገም፤ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ ሄዶ በወኅኒ አሳሰረው። 31 ባልንጀሮቹ ባርያዎችም ያደረገውን ሁሉ አይተው እጅግ አዘኑ፤ መጥተውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ነገሩት። 32 ከዚያ በኋላ ጌታው ጠርቶ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ ባርያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውሁልህ፤ 33 እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህን ልትምረው አይገባህም ነበርን?’ 34 ጌታውም ተቆጥቶ ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ለሚያሠቃዩት አሳልፎ ሰጠው። 35 ከእናንተም እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ የሰማዩ አባቴ ደግሞ እንዲሁ ያደርግባችኋል።” |