ማቴዎስ 16 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ተአምር ለማየት የቀረበ ጥያቄ ( ማር. 8፥11-13 ፤ ሉቃ. 12፥54-56 ) 1 ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሊፈትኑት መጡና ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። 2 እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ሲመሽ ‘ሰማዩ ቀልቶአልና ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ። 3 ጠዋት ደግሞ ‘ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን ገጽታ መለየት ታውቃላችሁ፤ የዘመኑን ምልክት ግን መለየት አትችሉም። 4 ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም።” ከዚህ በኋላ ትቶአቸው ሄደ። የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን እርሾ ( ማር. 8፥14-21 ) 5 ደቀመዛሙርቱ ወደ ማዶ በሚሻገሩበት ጊዜ እንጀራ መያዝን ረስተው ነበር። 6 ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” አላቸው። 7 እነርሱም እርስ በርሳቸው “እንጀራ ስላልያዝን ነው” ብለው አሰቡ። 8 ኢየሱስም ይህንን አውቆ እንዲህ አላቸው “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እንጀራ ስላልያዛችሁ ለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? 9 አሁንም አታስተውሉምን? አምስቱ እንጀራ ለአምስት ሺህ በቅቶ ስንት መሶብ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? 10 እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺህ በቅቶ ስንት ቅርጫት እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? 11 ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉም? ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ።” 12 ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠነቀቁ እንዳልነገራቸው ተገነዘቡ። ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን ጴጥሮስ መግለጡ ( ማር. 8፥27-30 ፤ ሉቃ. 9፥18-21 ) 13 ኢየሱስ ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ ወደሚባል አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?” ብሎ ጠየቃቸው። 14 እነርሱም “አንዳንዶቹ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎች ኤልያስ፥ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት። 15 እርሱም “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። 16 ስምዖን ጴጥሮስም “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ መለሰ። 17 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! የተባረክህ ነህ! በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና። 18 እኔም እልሃለሁ፤ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚችም ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይነግሱባትም። 19 የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈታው በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” 20 ከዚህ በኋላ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ለማንም እንዳይናገሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ኢየሱስ ስለሚደርስበት መከራና ሞት እንደ ተናገረ ( ማር. 8፥31-33 ፤ ሉቃ. 9፥22-27 ) 21 ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንዳለበት ከሽማግሌዎች፥ ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ብዙ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል በሦስተኛውም ቀን እንደሚነሣ ለደቀ መዛሙርቱ ይነግራቸው ጀመር። 22 ጴጥሮስም ገለል አድርጎ ወስዶ “ጌታ ሆይ! ይህ ከቶ አይድረስብህ” ብሎ ይገሥጸው ጀመር። 23 እርሱ ግን ዞሮ ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፤ አንተ ሰይጣን! ለእኔ ዕንቅፋት ነህ፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና።” አለው። 24 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው “ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፥ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። 25 ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ግን ያገኛታል። 26 ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? 27 የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣልና፤ በዚያን ጊዜ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይከፍለዋል። 28 እውነት እላችኋለሁ፥ እዚህ ከቆሙት መካከል የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።” |