ሚልክያስ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የሚመጣው መልዕክተኛ 1 እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፤ የምትደሰቱበትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 2 እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና፤ የሚመጣበትን ቀን መቋቋም የሚችል ማን ነው? እርሱስ ሲገለጥ የሚቆም ማን ነው? 3 ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፥ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፥ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቁርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ። 4 በዚያ ጊዜ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ቁርባን እንደ ዱሮው ዘመንና እንደ ቀደሙት ዓመታት ጌታን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። 5 ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በአስማተኞች፥ በዘማውያን፥ በሐሰት በሚምሉ፥ የሠራተኛውን ደመወዝ በሚያስቀሩ፥ መበለቲቱንና የሙት ልጅን በሚያስጨንቁ፥ ስደተኛውን በሚገፉ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 6 እኔ ጌታ አልለወጥምና፤ ስለዚህ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ አልጠፋችሁም። 7 ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከትእዛዜ ርቃችኋል፥ አልጠበቃችሁትምም። ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። እናንተ ግን፦ የምንመለሰው እንዴት ነው? ብላችኋል። እግዚአብሔርን አትዝረፉ 8 ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን ሰርቃችሁኛል። እናንተም፦ እንዴት እንሰርቅሃለን? ብላችኋል። በአሥራትና በቁርባን ነው። 9 እናንተ፥ ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ ሰርቃችሁኛልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ። 10 በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አስገቡ፤ የሰማያቶችን መስኮቶች ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 11 ስለ እናንተ በላተኛውን እገሥጻለሁ፥ የአፈራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁ ያለውንም ወይን ፍሬውን አያረግፍም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 12 ሕዝቦች ሁሉ የተባረኩ ብለው ይጠሩአችኋል፥ የደስታ ምድር ትሆናላችሁና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 13 በእኔ ላይ የድፍረት ቃላትን ተናግራችኋል፥ ይላል ጌታ። እናንተ ግን፦ በአንተ ላይ የተናገርነው ምንድነው? ትላላችሁ። 14 እናንተም እንዲህ ብላችኋል፦ እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ ትእዛዙን መጠበቅ፥ በሠራዊት ጌታ ፊት ኀዘንተኞች ሆነን መሄድ ምን ይጠቅመናል? 15 አሁንም ትዕቢተኞችን የተባረኩ ብለን እንጠራቸዋለን፤ ክፉንም የሚሠሩ ታንጸዋል፥ እግዚአብሔርንም ይፈታተናሉ፥ ያመልጣሉም። የታማኝ ሰው ሽልማት 16 በዚያን ጊዜ ጌታን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ ጌታም አደመጠ፥ ሰማም፥ ጌታን ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያከብሩ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ። 17 እነርሱ የእኔ ይሆናሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ እኔ በምሠራበት ቀን፥ ሰው የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚምር፥ እንዲሁ እምራቸዋለሁ። 18 ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፥ እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት ታያላችሁ። |