Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ሚልክያስ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 “ካህናት ሆይ፥ አሁንም ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው።

2 “ባትሰሙ፥ ለስሜም ክብር ለመስጠት በልባችሁ ባታኖሩት፥” ይላል የሠራዊት ጌታ፥ “እርግማን እልክባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማለሁ፤ አሁንም ረግሜዋለሁ ምክንያቱም በልባችሁ አላደረጋችሁትምና።”

3 እነሆ፥ ዘራችሁን እገሥጻለሁ፥ በፊታችሁ ላይ ፈርስን እበትናለሁ፥ ይህም ፈርስ ለበዓላችሁ መሥዋዕት ካመጣችኋቸው ነው፤ እናንተንም ከእርሱ ጋር ያነሳችኋል።

4 ቃል ኪዳኔ ከሌዊ ጋር ለማድረግ ይህን ትእዛዝ እንደ ላክሁላችሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።

5 ቃል ኪዳኔ ከእርሱ ጋር የሕይወትና የሰላም ነበረ፤ እንዲያከብረኝ እነርሱን ሰጠሁት፤ እርሱም አከበረኝ፥ ከስሜም በማክበር ፈራኝ።

6 የእውነት ትምህርት በአፉ ውስጥ ነበረ፥ በከንፈሩም ውስጥ ስሕተት አልተገኘም፤ ከእኔ ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፥ ብዙዎችንም ከኃጢአት መለሰ።

7 የካህን ከንፈሮች ዕውቀትን መጠበቅ አለባቸው፤ ሰዎችም ሕግን ከአፉ መፈለግ አለባቸው፤ ምክንያቱም የሠራዊት ጌታ መልእክተኛ ነው።

8 እናንተ ግን ከመንገዱ ተለይታችኋል፤ በሕግም ብዙዎችን አሰናክላችኋል፤ የሌዊንም ቃል ኪዳን አፍርሳችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።

9 ስለዚህ መንገዴን ስላልጠበቃችሁ፥ በሕግም ለሰው ፊት እንዳዳላችሁ መጠን፥ እኔ ደግሞ በሕዝብ ሁሉ ፊት የተናቃችሁና የተዋረዳችሁ አድርጌአችኋለሁ።


ቃል ኪዳኑ በይሁዳ ረከሰ

10 የሁላችን አባት አንድ አይደለምን? የፈጠረንስ አንድ አምላክ አይደለምን? የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን ለማርከስ ሁላችንም ለምን ወንድማችንን እናታልላለን?

11 ይሁዳ አታልሎአል፥ በእስራኤልና በኢየሩሳሌም ውስጥ ርኩሰት ሠርቷል፤ ይሁዳ ጌታ የወደደውን መቅደስ አርክሶአል፥ የባዕድንም አምላክ ልጅ አግብቶአል።

12 ይህን ከሚያደርግ ሰው፥ የሚጠራውንና የሚመልሰውን ለሠራዊትም ጌታ ቁርባን የሚያቀርበውን ከያዕቆብ ድንኳን ያጠፋል።

13 ይህንም ደግሞ አድርጋችኋል፤ እግዚአብሔር ቁርባኑን ዳግመኛ እንዳይመለከት፥ ከእጃችሁም በደስታ እንዳይቀበለው መሠዊያውን በእንባና በልቅሶ በኅዘንም ትከድናላችሁ።

14 እናንተም፦ ለምን ይህ ሆነ? ትላላችሁ። ምክንያቱም ሚስትህን አታልለሃታልና ጌታ በአንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለ ሆነ ነው፤ እርሷም ጓደኛህና የቃል ኪዳን ሚስትህ ነበረች።

15 አንድ አላደረጋቸውምን? የመንፈስም ቅሪት ለእርሱ ነው? አንዱስ ምን ፈልጎ ነው? የእግዚአብሔርን ዘር ፈልጎ ነው። ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፥ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል።

16 መፋታትን እጠላለሁና፥ ይላል ጌታ የእስራኤል አምላክ፥ ልብሱንም በሁከት የሚሸፍንን ሰው እጠላለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ ስለዚህ እንዳታታልሉ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ።

17 በቃላችሁ ጌታን አሰልችታችሁታል። እናንተም፦ እርሱን ያሰለቸነው በምንድን ነው? ትላላችሁ። “ክፉን የሚያደርግ ሁሉ በጌታ ፊት መልካም ነው፥ እርሱም በእነርሱ ደስ ይለዋል” ወይም “የፍትሕ አምላክ የት አለ?” በማለታችሁ ነው።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች