Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ሉቃስ 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የኢየሱስ መፈተን
( ማቴ. 4፥1-11 ፤ ማር. 1፥12-13 )

1 ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ተመለሰ፤ በምድረ በዳም በመንፈስ ተመራ።

2 ለአርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ። በእነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፤ ቀኖቹም በተፈጸሙ ጊዜ ተራበ።

3 ዲያብሎስም፦ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዝ፤” አለው።

4 ኢየሱስም፦ “ ‘ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤” ብሎ መለሰለት።

5 ዲያብሎስም ከፍ ወዳለው ስፍራ አውጥቶት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው።

6 ዲያብሎስም፦ “ለአንተ ይህን ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውንም እሰጥሃለሁ፤ ለእኔ ተሰጥተቶአልና ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁ፤

7 ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል፤” አለው።

8 ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤” አለው።

9 ወደ ኢየሩሳሌም ደግሞ ወሰደው፤ በመቅደስም ጫፍ ላይ አቆመው፥ እንዲህም አለው፦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ ከዚህ ወደ ታች ራስህን ወርውር፤

10 እነሆ፥ ‘አንተን ለመጠበቅ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤

11 እግርህም በድንጋይ ከቶ እንዳይሰናከል አንተን በእጃቸው ያነሡሃል፤’ ተብሎ ተጽፎአልና።”

12 ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ጌታን አምላክህን አትፈታተነው፤’ ተብሏል፤” አለው።

13 ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ለጊዜው ከእርሱ ተለየ።


ኢየሱስ የማስተማር ሥራውን በገሊላ መጀመሩ
( ማቴ. 4፥12-17 ፤ ማር. 1፥14-15 )

14 ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለው አገር ሁሉ ተወራ።

15 እንዲሁም በሁሉም እየተመሰገነ በምኵራባቸው ያስተምር ነበር።

16 ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደተለመደው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ።

17 የነቢዩም የኢሳይያስ ጥቅል ብራና ተሰጠው፤ ጥቅሉንም በዘረጋው ጊዜ፥ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ፤

18 “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች መልካም ዜናን እንዳበሥር ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዐይነ ስውሮችም ማየትን እንዳውጅ፥ የተጨቆኑትንም ነጻ እንዳወጣ

19 የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል።”

20 ጥቅል ብራናውንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መልሶ ከሰጠ በኋላ ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኩር ብለው ይመለከቱት ነበር።

21 እርሱም፦ “ዛሬ ይህ በጆሮዎቻችሁ የሰማችሁት ጽሑፍ ተፈጸመ፤” ይላቸው ጀመር።

22 ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር፤ ከአፉም ከሚወጡት ቃላት ጸጋ የተነሣ እየተደነቁ፦ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር።

23 እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ያለ ምንም ጥርጥር ይህንን ምሳሌ ትጠቅሱብኛላችሁ ‘አንተ ሐኪም! እስቲ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም እንዳደረግህ የሰማናቸውን ነገሮች ሁሉ፥ በዚህ በገዛ አገርህ ደግሞ አድርግ።’ ”

24 እንዲህም አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፤ አንድም ነቢይ በገዛ አገሩ ተቀባይነት የለውም።

25 ነገር ግን በእውነት እላችኋለሁ፤ በኤልያስ ዘመን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ተዘግቶ ሳለ፥ በምድር ሁሉ ላይ ብርቱ ራብ በነበረ ጊዜ፥ በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፤

26 ቢሆንም ግን ኤልያስ ወደ ሲዶናዊቷ መበለት ወደ ሰራፕታ እንጂ ወደ ሌሎቹ ወደ አንዳቸውም አልተላከም።

27 በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነርሱ ማንም አልነጻም።”

28 በምኵራብም ውስጥ የነበሩ ሁሉ እነዚህን ነገሮች በሰሙ ጊዜ በቁጣ ተሞሉ፤

29 ተነሥተውም ከከተማይቱ ውጭ አወጡት፤ ገፍትረውም ሊጥሉት ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ኮረብታ አፋፍ ላይ ወሰዱት፤

30 እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።


ኢየሱስ ርኩስ መንፈስ ያደረበትን ሰው መፈወሱ
( ማር. 1፥21-28 )

31 የገሊላ ከተማም ወደ ሆነችው ወደ ቅፍርናሆም ወረደ። በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር፤

32 ቃሉ በሥልጣን ተሞልቶ ነበርና በትምህርቱ ተገረሙ።

33 በምኵራብም የርኩስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፤ በታላቅ ድምፅም ጮኾ፦

34 “ተው፤ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኛ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደሆንህ አውቄሃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ፤” አለ።

35 ኢየሱስም፦ “ዝም በል፤ ከእርሱም ውጣ፤” ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በመካከላቸው ጥሎት ምንም ሳይጐዳው ከእርሱ ወጣ።

36 ሁሉም ተደነቁ፤ እርስ በርሳቸውም፦ “ይህ ቃል ምንድነው? በሥልጣንና በኃይል ርኩሳን መናፍስትን ያዝዛል፥ እነርሱም ይወጣሉ፤” እያሉ ይነጋገረሩ ነበር።

37 ስለ እርሱም የተነገረው በዙሪያው ባለው አገር፥ በሁሉ ስፍራ ተሰራጭቶ ነበር።


ኢየሱስ የጴጥሮስን አማት እና ብዙ ሕመምተኞችን መፈወሱ
( ማቴ. 8፥14-17 ፤ ማር. 1፥29-34 )

38 ከምኵራብም ተነሥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም አማት በብርቱ ትኩሳት ታማ ነበር፤ ስለ እርሷም ለመኑት።

39 በአጠገብዋም ቆሞ ትኩሳቱን ገሠጸውና ለቀቃት፤ ወዲያውም ተነሥታ አገለገለቻቸው።

40 ፀሐይም ስትጠልቅ ሰዎች በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙባቸውን ሕሙማን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም በእያንዳንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው።

41 አጋንንትም ደግሞ፦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤” ብለው እየጮኹ ከብዙዎች ይወጡ ነበር፤ እርሱ ግን ገሠጻቸው፤ እንዲናገሩም አልፈቀደላቸውም፥ ምክንያቱም ክርስቶስ እንደሆነ አውቀውት ነበርና።

42 ሲነጋም ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ይፈልጉት ነበር፤ ወደ እርሱም መጡ፤ ከእነርሱም ተለይቶ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ይጥሩ ነበር።

43 እርሱ ግን፦ “የተላክሁት በዚሀ ምክንያት ነውና ለሌሎቹ ከተማዎችም የእግዚአብሔርን መንግሥት መልካም ዜና ማብሠር ይገባኛል፤” አላቸው።

44 እርሱም በይሁዳ በሚገኙት ምኵራቦች ይሰብክ ነበር።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች