ዘሌዋውያን 9 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)አሮን የክህነት አገልግሎቱን መጀመሩ 1 በስምንተኛውም ቀን እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ አሮንንና ልጆቹን የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ጠራ። 2 አሮንንም እንዲህ አለው፦ “ከመንጋው ነውር የሌለባቸውን ለኃጢአት መሥዋዕት እምቦሳውን፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አውራውን በግ ወስደህ በጌታ ፊት አቅርብ። 3 ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ትናገራለህ፦ ‘ለኃጢአት መሥዋዕት አውራ ፍየልን፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት ነውር የሌለባቸውን አንድ ዓመት የሆናቸውን እምቦሳና ጠቦትን፥ 4 ለአንድነትም መሥዋዕት በሬንና አውራን በግ፥ በዘይትም የተለወሰ የእህልን ቁርባን በጌታ ፊት ለመሠዋት ውሰዱ፥ ዛሬ ጌታ ተገልጦላችኋልና።’ ” 5 ሙሴም ያዘዛቸውን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አመጡ፤ ማኅበሩም ሁሉ ቀርበው በጌታ ፊት ቆሙ። 6 ሙሴም፦ “የጌታም ክብር እንዲገለጥላችሁ ጌታ እንድታደርጉት ያዘዘው ይህን ነገር ነው፤” አለ። 7 ሙሴም አሮንን፦ “ወደ መሠዊያው ቅረብ፥ የኃጢአትህንም መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፥ ለራስህና ለሕዝቡም አስተስርይ፤ ጌታም እንዳዘዘ የሕዝቡን ቁርባን አቅርብ አስተስርይላቸውም” አለው። 8 አሮንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ስለ ራሱ ኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን እምቦሳ አረደ። 9 የአሮንም ልጆች ደሙን አቀረቡለት፤ ጣቱንም በደሙ ውስጥ ነክሮ የመሠዊያውን ቀንዶች ቀባ፥ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው። 10 ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ከኃጢአቱ መሥዋዕት ስቡንና ኩላሊቶቹን፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ። 11 ሥጋውንና ቆዳውንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። 12 የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አረደ፤ የአሮንም ልጆች ደሙን አመጡለት፥ እርሱም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ረጨው። 13 በየብልቱም የተሸነሸነውን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ከጭንቅላቱ ጋር አመጡለት፤ እርሱም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 14 የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም አጠበ፤ በመሠዊያውም ባለው የሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው። 15 ከዚያም በኋላ የሕዝቡን ቁርባን አቀረበ፤ ስለ ሕዝቡ ለኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን ፍየል ወስዶ አረደው፥ ስለ ኃጢአትም እንደ ፊተኛው የኃጢአት መሥዋዕት ሠዋው። 16 እንደ ሥርዓቱም አድርጎ የሚቃጠለውን መሥዋዕትም አቀረበ። 17 የእህሉንም ቁርባን አቀረበ፥ ከእርሱም እፍኝ ሙሉ ወስዶ በጥዋት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት አጠገብ በመሰዊያው ላይ አቃጠለው። 18 ስለ ሕዝቡ የአንድነት መሥዋዕት የሚቀርበውን በሬውንና አውራውን በግ አረደ፤ የአሮንም ልጆች ደሙን አመጡለት፥ በመሠዊያውም ላይ በዙሪያው ረጨው፤ 19 የበሬውንና የአውራውንም በግ ስብ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ ኩላሊቶቹንም፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ አመጡለት። 20 ስቡንም በፍርምባዎቹ ላይ አደረጉ፥ እርሱም ስቡን በመሠዊያው ላይ አቃጠለ፤ 21 ሙሴም እንደ ታዘዘው አሮን ፍርምባዎቹንና ቀኝ ወርቹን በጌታ ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ወዘወዘ። 22 አሮንም እጆቹን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ ባረካቸውም፤ እርሱም የኃጢአቱንና የሚቃጠለውን የሰላሙንም መሥዋዕት ከሠዋ በኋላ ወረደ። 23 ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ገቡ፤ በወጡም ጊዜ ሕዝቡን ባረኩ፤ የጌታም ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ። 24 እሳትም ከጌታ ዘንድ ወጣ፥ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ስቡንም በላ፤ ሕዝቡም ሁሉ አይተው እልል አሉ፥ በግምባራቸውም ተደፍተው ሰገዱ። |