ዘሌዋውያን 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የካህን የሹመት ሥርዓት 1 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “አሮንን፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹን፥ ልብሱንም፥ የቅባቱንም ዘይት፥ ለኃጢአት መሥዋዕትም የሚቀርበውን ወይፈን፥ ሁለቱንም አውራ በጎች፥ እርሾ ያልነካው ቂጣ የሚቀመጥበትንም መሶብ ውሰድ፤ 3 ማኅበሩንም ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስብ።” 4 ሙሴም ጌታ እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተሰበሰበ። 5 ሙሴም ማኅበሩን፦ “ጌታ እንዲደረግ ያዘዘው ነገር ይህ ነው” አላቸው። 6 ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፥ በውኃም አጠባቸው። 7 ልብስም አለበሰው፥ በመርገፍም በተጌጠ ዝናር አስታጠቀው፥ ቀሚስም አለበሰው፥ ኤፉድም ደረበለት፥ በብልሃትም በተጠለፈ የኤፉድ ማንጠልጠያ አስታጠቀውና በእርሱ ላይ ኤፉዱን አሰረው። 8 የደረት ኪስ በእርሱ ላይ አደረገ፤ በደረቱ ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን አኖረበት። 9 ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው በራሱ ላይ መጠምጠሚያውን አደረገ፤ በመጠምጠሚያውም ላይ በፊቱ በኩል፥ የወርቅ ጉንጉን ሆኖ በቅጠል መልክ የተሠራውን የተቀደሰ አክሊል፥ አደረገ። 10 ሙሴም የቅባቱን ዘይት ወሰደ፥ ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሳቸው። 11 ከእርሱም በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ እንዲቀደሱም መሠዊያውንና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሳሕንና መቀመጫውን ቀባ። 12 ከቅባቱም ዘይት በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፥ እንዲቀደስም ቀባው። 13 ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ የአሮንን ልጆች አቀረበ፥ ቀሚሶችንም አለበሳቸው፥ በመርገፍም በተጌጠ መታጠቂያ አስታጠቃቸው፥ ቆብም ደፋባቸው። 14 የኃጢአትንም መሥዋዕት ወይፈን አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በኃጢአቱ መሥዋዕት ወይፈን ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 15 አረደውም፤ ሙሴም ደሙን ወስዶ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ዙሪያ ቀባ፥ መሠዊያውንም አነጻው፤ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው፥ እንዲያስተሰርይለትም ቀደሰው። 16 በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች ከስባቸው ጋር ወሰደ፤ ሙሴም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 17 ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ወይፈኑን፥ ቆዳውንም፥ ሥጋውንም፥ ፈርሱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። 18 ለሚቃጠል መሥዋዕትም የሚሆን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 19 አረደውም፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨው። 20 አውራውንም በግ በየብልቱ ቈረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን ብልቶቹንም ስቡንም አቃጠለ። 21 የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠበ፤ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን፥ መዓዛው ያማረ ሽታ የሆነ፥ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ሙሴ አውራውን በግ ሁሉ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 22 ለቅድስናም የሚሆነውን ሁለተኛውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 23 አረደውም፤ ሙሴም ከደሙ ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት አስነካው። 24 የአሮንንም ልጆች አቀረበ፤ ሙሴም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣት ከደሙ አስነካ፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨ። 25 ከዚያም በኋላ ስቡንና ላቱን፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች ስባቸውንም፥ ቀኝ ወርቹንም ወሰደ፤ 26 በጌታ ፊት ካለው እርሾ ያልነካው ቂጣ ከሚቀመጥበት መሶብ አንድ እርሾ ያልገባበት የቂጣ እንጐቻ፥ አንድም ከዘይት ጋራ የተሰናዳ የቂጣ እንጐቻ፥ አንድም ስስ ቂጣ ወስዶ በስቡና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖራቸው። 27 ሁሉንም በአሮንና በልጆቹ እጆች ላይ አደረገ፥ በጌታም ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ወዘወዛቸው። 28 ከዚያም በኋላ ለጌታ በእሳት የሚቀርብ ቁርባን፥ መዓዛው ያማረ ሽታ የሆነ፥ የቅድስና መሥዋዕት አድርጎ ሙሴ ከእጃቸው ተቀብሎ በሚቃጥለው መሥዋዕት ላይ በመሠዊያው አቃጠለው። 29 ሙሴም ፍርምባውን ወስዶ በጌታ ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ወዘወዘው፤ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ይህ ለቅድስና ከሚቀርበው አውራ በግ የሆነ የሙሴ ድርሻ ነበር። 30 ሙሴም ከቅባቱ ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ከደሙ ወስዶ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ በልጆቹና በልጆቹ ልብስ ላይ ረጨው፤አሮንንና ልብሱንም፥ ልጆቹንም፥ የልጆቹንም ልብስ ቀደሰ። 31 ሙሴም አሮንንና ልጆቹን እንዲህ አላቸው፦ “ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉ፤ ከዚህም ጋር ‘አሮንና ልጆቹ ይበሉታል’ ብዬ እንዳዘዝሁ የቅድስናው መሥዋዕት እንጀራ ከሚቀመጥበት መሶብ ውስጥ ያለውን እንጀራ በዚያ ትበሉታላችሁ። 32 ከሥጋውና ከእንጀራውም የተረፈውን በእሳት ታቃጥሉታላችሁ። 33 እናንተን በቅድስና ማዕረግ ለመሾም ሰባት ቀን ይወስዳልና የክህነታችሁ ቀን እስኪፈጸም ድረስ ሰባት ቀን ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትውጡ። 34 ዛሬ እንደተደረገው እንዲሁ ለእናንተ ማስተስረያም እንዲደረግ ጌታ አዝዞአል። 35 እንዳትሞቱም የጌታን ትእዛዝ እየጠበቃችሁ፥ ለሰባት ቀን ሌሊትና ቀን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ትቀመጣላችሁ፤ እኔ እንዲህ ታዝዣለሁና።” 36 አሮንና ልጆቹም ጌታ በሙሴ አንደበት ያዘዘውን ቃላት ሁሉ አደረጉ። |