Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘሌዋውያን 25 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ሰባተኛው ዓመት

1 ጌታም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

2 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ምድሪቱ ለጌታ ሰንበት ታድርግ።

3 ስድስት ዓመት እርሻህን ትዘራለህ፥ ስድስት ዓመትም የወይን ተክልህን ግረዝ ፍሬዋንም ሰብስብ።

4 በሰባተኛው ዓመት ግን ለጌታ ሰንበት፥ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ይሁን፤ በእርሻህ ላይ አትዝራ፥ የወይን ተክልህንም አትግረዝ።

5 በመከርህ ማንም ሰው ሳይዘራው የበቀለውን አትሰብስብ፥ ያልተገረዘውን የወይንህን ተክል ፍሬ አታከማች፤ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ዓመት ይሁን።

6 የምድሪቱ ሰንበት ለእናንተ፥ ለአንተም፥ ለወንድ ባርያህም፥ ለሴት ባርያህም፥ ተቀጥሮ ለሚያገለግልህም፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ትሰጣችኋለች።

7 እንዲሁም ለእንስሶችህ፥ በምድርህም ላሉት አራዊት እርሷ የምትሰጠው ሁሉ ለመኖ ይሆናል።


የኢዮቤልዩ ዓመት

8 “ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመት አድርገህ በዓመታት ውስጥ ያሉትን ሰንበታት ቁጠር፤ የዓመታቱም የሰንበታት ዘመን አርባ ዘጠኝ ዓመት ይሆኑልሃል።

9 ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን የቀንደ መለከትን ድምፅ ከፍ አድርገህ ታሰማለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ የቀንደ መለከትን ድምፅ ታሰማላችሁ።

10 ኀምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፥ በምድሪቱም ለሚኖሩባት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእንናተ ኢዮቤልዩ ይሆናል፤ ከእናንተም እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለሳል።

11 ያ ኀምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ዓመት ይሆናል፤ በእርሱም አትዝሩ፥ እንዲሁም ማንም ሰው ሳይዘራው የበቀለውን አትሰብስቡ፥ ያልተገረዘውን የወይን ተክል ፍሬ አታከማቹ።

12 ኢዮቤልዩ ነውና የተቀደሰ ይሁንላችሁ፤ ምድሪቱ ራስዋ የምትሰጠውን ፍሬ ትበላላችሁ።

13 “በዚህ በኢዮቤልዩ ዓመት እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱ ይመለሳል።

14 ለባልንጀራህም መሬት ብትሸጥ፥ ወይም ከባልንጀራህ እጅ ብትገዛ፥ አንዱ ሌላውን አያታልል።

15 ከኢዮቤልዩ በኋላ እንደ ዓመታቱ ቍጥር ከባልንጀራህ ትገዛለህ፤ እርሱም እንደ መከሩ ዓመታት ቍጥር ይሸጥልሃል።

16 እርሱ እንደ መከሩ ቍጥር ይሸጥልሃልና ዓመታቱ ብዙ በሆኑ ቍጥር ዋጋውን ከፍ ታደርጋለህ፥ ዓመታቱ ግን ባነሱ ቍጥር ዋጋውን ታሳንሳለህ።

17 እኔም ጌታ አምላካችሁ ነኝና ሰው ባልንጀራውን አያታልል፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።

18 “ሥርዓቶቼን አድርጉ፥ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ላይ በደኅንነት ትቀመጣላችሁ።

19 ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፥ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርሷም ላይ በደኅንነት ትቀመጣላችሁ።

20 ዳሩ ግን እናንተ፦ ‘ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?’ ብትሉ፥

21 እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በእናንተ ላይ አዝዛለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች።

22 በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ቀድሞ ከተመረተው እህል ትበላላችሁ፤ የእርሷ ፍሬ እስከሚገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ቀድሞ ከተመረተው እህል ትበላላችሁ።

23 ምድሪቱም የእኔ ናትና፥ እናንተም ከእኔ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድሪቱን ለዘለዓለም አትሽጧት።

24 በርስት በያዛችሁት ምድር ሁሉ መቤዠትን ለምድሪቱ ታደርጋላችሁ።

25 “ወንድምህም ቢደኸይ ከርስቱም ቢሸጥ፥ የቅርብ ዘመዱ የሆነ ሰው መጥቶ ወንድሙ የሸጠውን ይቤዠዋል።

26 የሚቤዠውም ሰው ባይኖረው፥ እርሱም ቢበለጥግ፥ ለመቤዠትም የሚበቃ ቢያገኝ፥

27 እርሱም እስከ ሸጠበት ጊዜ ያሉትን ዓመታት ያሰላል፥ ከዚያም የቀረውን ወደ ገዛው ሰው ይመልሳል፤ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለሳል።

28 ለማስመለስ ግን በቂ ገንዘብ ባያገኝ፥ ሽያጩ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ በገዛው ሰው እጅ ይሆናል፤ በኢዮቤልዩ ዓመት ነፃ ይወጣል፥ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለሳል።

29 “ማናቸውም ሰው ቅጥር ባለው ከተማ ውስጥ ያለ መኖሪያ ቤትን ቢሸጥ፥ ከተሸጠ በኋላ አንድ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ለመቤዠት ይችላል፤ ለአንድ ሙሉ ዓመት የመቤዠት መብት አለውና።

30 አንድ ዓመትም እስከሚፈጸም ባለው ጊዜ ሁሉ ባይቤዠው፥ ቅጥር ባለው ከተማ ውስጥ ያለው ቤት ለገዛው ሰው ለልጅ ልጁ ለዘለዓለም ይጸናለታል፤ በኢዮቤልዩም ከእርሱ ነፃ አይወጣም።

31 ነገር ግን በዙሪያቸው ቅጥሮች በሌላቸው መንደሮች ያሉ ቤቶች እንደ እርሻ መሬቶች ይቈጠራሉ፤ ይቤዣሉ፥ በኢዮቤልዩም ነፃ ይወጣሉ።

32 ነገር ግን ለሌዋውያን ርስታቸው በሆኑት በሌዋውያን ከተሞች ውስጥ ያሉትን ቤቶች ለዘለዓለም የመቤዠት መብት አላቸው።

33 ማናቸውም ሰው ከሌዋውያን ቤት ቢገዛ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል በሌዋውያን ከተሞች ያሉ ቤቶች ለሌዋውያን ርስቶቻቸው ናቸውና በርስታቸው ከተማ ውስጥ የተሸጠው ቤት በኢዮቤልዩ ይመለሳል።

34 በከተማቸውም ዙሪያ ያለው መሰማሪያ የዘለዓለም ርስታቸው ነውና አይሸጥም።

35 “ወንድምህ ቢደኸይ፥ እርሱም በአንተ ዘንድ ራሱን መቻል ቢያቅተው፥ አጽናው፤ እንደ እንግዳና እንደ መጻተኛም ከአንተ ጋር ይኑር።

36 ወንድምህ ከአንተ ጋር እንዲኖር ከእርሱ ምንም ወለድ ወይም ትርፍ አትውሰድ፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።

37 ብርህን በወለድ አታበድረው፤ ምግብህንም በትርፍ አትሽጥለት።

38 የከነዓንን ምድር እንድሰጣችሁ፥ አምላክም እንድሆናችሁ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።

39 “በአንተም ዘንድ ያለው ወንድምህ ቢደኸይ ራሱንም ለአንተ ቢሸጥ፥ እንደ ባርያ እንዲያገለግል አታድርገው።

40 ይልቁንም እርሱ እንደ ተቀጣሪ አገልጋይ እና እንደ መጻተኛ ከአንተ ጋር ይሁን፤ እስከ ኢዮቤልዩም ዓመት ያገልግልህ።

41 ከዚያም በኋላ እርሱ ከልጆቹ ጋር ከአንተ ነፃ ይወጣል፥ ወደ ወገኖቹም ወደ አባቱም ርስት ይመለሳል።

42 ስለዚህ ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው ባርያዎቼ ናቸውና እንደ ባርያዎች አይሸጡ።

43 በጽኑ እጅ አትግዛው፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።

44 ወንድ ባርያና ሴት ባርያ እንዲኖራችሁ ብትፈልጉ ግን በዙሪያችሁ ካሉት አሕዛብ መካከል ወንድና ሴት ባርያዎች ትገዛላችሁ።

45 እንዲሁም በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት መጻተኞች፥ በምድራችሁም ውስጥ ከወለዱአቸው ከእናንተ ጋር ካሉት ከቤተሰቦቻቸው ውስጥ ባርያዎችን ትገዛላችሁ፤ ርስትም ይሆኑላችኋል።

46 ከእናንተም በኋላ ልጆቻችሁ ለዘለዓለም እንዲወርሱአቸው ተዉአቸው፤ እነርሱን ባርያዎች ታደርጋላችሁ፥ ነገር ግን የእስራኤል ልጆች ወንድሞቻችሁ ናቸውና አንዱ ሌላውን በጽኑ እጅ አይግዛው።

47 “በአንተም ዘንድ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆን፥ ወንድምህም በእርሱ አጠገብ ቢደኸይ፥ ራሱንም ለመጻተኛው ወይም በአንተ ዘንድ ለተቀመጠው እንግዳ ወይም ለመጻተኛው የቤተሰብ አባላት ቢሸጥ፥

48 ከተሸጠ በኋላ መቤዠት ይችላል፤ ከወንድሞቹ አንዱ ይቤዠው፤

49 ወይም አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ይቤዠው፤ ወይም ከወገኑ የሥጋ ዘመዱ የሆነ ሰው ይቤዠው፤ ወይም እርሱ ቢበለጥግ ራሱን ይቤዥ።

50 ከገዛውም ሰው ጋር ለገዢው ራሱን ከሸጠበት ዓመት ጀምሮ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ያለውን ጊዜ ያሰላል፤ የሽያጩም ብር እንደ ዓመታቱ ቍጥር ይሆናል፤ ከባለቤቱም ጋር የነበረበት ጊዜ ተቀጣሪ አገልጋይ እንደ ነበረበት ጊዜ ተደርጎ ይተመናል።

51 ብዙ ዓመታትም ቢቀሩ እንደ እነርሱ ቍጥር ከሽያጩ ብር የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ።

52 እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ጥቂቶች ዓመታት ቢቀሩ ከእርሱ ጋር በመሆን ያሰላል፤ እርሱ ማገልገል እንደሚገባው የዓመታት መጠን የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ።

53 በእርሱ ዘንድ በየዓመቱ እንደሚቀጠር አገልጋይ ይሁን እንጂ በአንተ ፊት በጽኑ እጅ አይግዛው።

54 እርሱም በእነዚህ በማናቸውም መንገዶች ባይቤዥ፥ በኢዮቤልዩ ዓመት እርሱ ከልጆቹ ጋር ነፃ ይወጣል።

55 የእስራኤል ልጆች ለእኔ ባርያዎች ናቸውና፤ ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው ባርያዎቼ ናቸው፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።”

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች