Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘሌዋውያን 14 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


በሥጋ ደዌ የተጠቃውን ሰውና ቤቱን የማንጻት ሥርዓት

1 ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦

2 “በመንጻቱ ቀን የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው ሕግ ይህ ይሆናል፤ ወደ ካህኑ ይወስዱታል።

3 ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ለምጽ ካለበት ሰው ላይ ቢጠፋ፥

4 ካህኑ ስለሚነጻው ሰው በሕይወት ያሉ ሁለት ንጹሐን ወፎች፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም እንዲመጣለት ያዝዛል።

5 ካህኑም ከሁለቱ ወፎች አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ እንዲታረድ ያዝዛል።

6 በሕይወት ያለውን ወፍ፥ የዝግባውንም እንጨት፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ሂሶጱንም ወስዶ ይነክራቸዋል፥ በሕይወትም ያለውን ወፍ በምንጭ ውኃ ላይ በታረደው የወፍ ደም ውስጥ ይዘፍቀዋል።

7 ከለምጽ ደዌ በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጨዋል፤ ከዚያም ንጹሕ ነህ ይለዋል፥ በሕይወትም ያለውን ወፍ በተንጣለለው ሜዳ ላይ እንዲበር ይለቀዋል።

8 የነጻውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ጠጉሩንም ሁሉ ይላጫል፥ በውኃም ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል፥ ነገር ግን ከድንኳኑ በውጭ ሆኖ ሰባት ቀን ይቀመጣል።

9 በሰባተኛውም ቀን ጠጉሩን ሁሉ ይላጫል፤ ራሱንም፥ ጢሙንም፥ ቅንድቡንም፥ የገላውንም ጠጉር ሁሉ ይላጫል፤ ከዚያም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፤ እርሱም ንጹሕ ይሆናል።

10 “በስምንተኛውም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባት ጠቦት፥ ነውር የሌለባትንም አንዲት የዓመት እንስት ጠቦት፥ ለእህሉም ቁርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ዘይትም ያለበትን አንድ የሎግ መስፈሪያ ይወስዳል።

11 የሚያነጻውም ካህን የሚነጻውን ሰውና እነዚህን ነገሮች በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በጌታ ፊት ያኖራቸዋል።

12 ካህኑም አንዱን ተባት ጠቦት ይወስዳል፤ እርሱንም ስለ በደል መሥዋዕት ያቀርበዋል፥ ጎን ለጎንም ዘይቱ ያለበትን የሎግ መስፈሪያውን፤ እነርሱንም ስለ መወዝወዝ ቁርባን በጌታ ፊት ይወዘውዛቸዋል።

13 የኃጢአትን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርድበት በተቀደሰው ስፍራ ጠቦቱን ያርደዋል፤ እንደ ኃጢአት መሥዋዕቱም እንዲሁ የበደል መሥዋዕቱ ለካህኑ ይሆናል፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ ነው።

14 ካህኑም ከበደል መሥዋዕት ደም ይወስዳል፤ እርሱም የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል።

15 ካህኑም ከሎግ መስፈሪያው ውስጥ ያለውን ዘይት ወስዶ በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያፈስሰዋል።

16 ካህኑም በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያለውን ዘይት በቀኝ ጣቱ ነክሮ ከዘይቱ በጌታ ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል።

17 ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ ከተረፈው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት፥ የበደልም መሥዋዕት በሆነው ደም ላይ ያስነካዋል።

18 ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ የተረፈውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርግበታል፤ ከዚያም ካህኑ በጌታ ፊት ያስተሰርይለታል።

19 ካህኑም የኃጢአቱን መሥዋዕት ያቀርባል፥ ከርኩሰቱም ለሚነጻው ሰው ያስተሰርይለታል፤ ከዚያም በኋላ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያርዳል።

20 ካህኑም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን በመሠዊያው ላይ ያቀርባል፤ እንዲህም አድርጎ ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ እርሱም ንጹሕ ይሆናል።

21 “ነገር ግን ድሀ ቢሆን ይህንንም ለማቅረብ በቂ ገንዘብ ባይኖረው፥ እንዲያስተሰርይለት ለበደል መሥዋዕት እንዲወዘወዝ አንድ ጠቦት፥ ለእህልም ቁርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ አንድ የሎግ መስፈሪያም ዘይት ይወስዳል።

22 ለመግዛትም አቅሙ የሚፈቅድለትን ያህል ሁለት ዋኖሶች ወይም የርግብ ግልገሎች፥ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያደርገዋል።

23 በስምንተኛውም ቀን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በጌታ ፊት ስለ መንጻቱ እንዲሆኑ ወደ ካህኑ ያመጣቸዋል።

24 ካህኑም የበደሉን መሥዋዕት ጠቦትና ዘይትም ያለበትን የሎግ መስፈሪያ ይወስዳል፤ ካህኑም ለመወዝወዝ ቁርባን በጌታ ፊት ይወዘውዛቸዋል።

25 የበደሉንም መሥዋዕት ጠቦት ያርዳል፤ ካህኑም ከበደሉ መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል።

26 ካህኑም ከዘይቱ በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያፈስሳል።

27 ካህኑም በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያለውን ዘይት በቀኝ ጣቱ ሰባት ጊዜ በጌታ ፊት ይረጨዋል።

28 ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ ካለው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት፥ የበደልም መሥዋዕት ደም ባረፈበት ስፍራ ላይ ያስነካዋል።

29 በጌታ ፊት እንዲያስተሰርይለት ካህኑ በእጁ መዳፍ ላይ የተረፈውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርገዋል።

30 ለመግዛትም አቅሙ የሚፈቅድለትን ያህል ከዋኖሶች ወይም ከርግብ ግልገሎች አንዱን ያቀርባል፤

31 አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ከእህል ቁርባን ጋር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፥ ካህኑም ለሚነጻው ሰው በጌታ ፊት ያስተሰርይለታል።

32 “ለመንጻቱ የሚቀርበውን ነገር መግዛት አቅሙ ለማይፈቅድለት የለምጽ ደዌ ላለበት ሰው ሕጉ ይህ ነው።”

33 ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦

34 “እኔ ወደምሰጣችሁ ርስት ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ በምትወርሱአት ምድር በአንድ ቤት ውስጥ የለምጽ ደዌ ባኖር፥

35 የቤቱ ባለቤት መጥቶ ካህኑን፦ ‘ደዌ የሚመስል ነገር በቤቴ ውስጥ ያለ ይመስለኛል’ ብሎ ይንገረው።

36 ካህኑም በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዳይረክስ፥ እርሱ ደዌውን ለማየት ወደ ቤቱ ከመግባቱ በፊት፥ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ያዝዛል፤ ከዚያም በኋላ ካህኑ ቤቱን ለማየት ይገባል።

37 ደዌውንም ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግድግዳ ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ ሆኖ ቢዥጐረጐር፥ መልኩም ከግድግዳው ውጫዊ ገጽታ ዘልቆ ቢገባ፥

38 ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ቤቱ በር ወጥቶ ሰባት ቀን ቤቱን ይዘጋዋል።

39 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ተመልሶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግድግዳ ላይ ቢሰፋ፥

40 ካህኑ ደዌ ያለባቸውን ድንጋዮች እንዲያወጡ፥ ከከተማውም ውጭ ወደ ረከሰው ስፍራ እንዲጥሉአቸው ያዝዛል።

41 የቤቱንም ውስጥ ዙሪያውን ያስፍቀዋል፤ የፋቁትንም የምርጊቱን አፈር ከከተማው ውጭ ወደ ረከሰ ስፍራ ያፈስሱታል።

42 በእነዚያም ድንጋዮች ስፍራ ሌሌች ድንጋዮችን አምጥተው ያገባሉ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይመርጉታል።

43 “ደዌውም ዳግም ቢመለስ፥ ድንጋዮቹም ከወጡ ቤቱም ከተፋቀና ከተመረገ በኋላ በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥

44 ካህኑ ገብቶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ውስት ቢሰፋ፥ በቤቱ ውስጥ ያለው እየሰፋ የሚሄድ የለምጽ ደዌ ነው፤ እርሱ ርኩስ ነው።

45 ቤቱንም፥ ድንጋዮቹንም፥ እንጨቱንም፥ የቤቱንም ምርጊት ሁሉ ያፈርሳል፤ እነርሱንም ከከተማው ውጭ ወደ ርኩስ ስፍራ ያወጣል።

46 በተዘጋበትም ጊዜ ሁሉ ወደ ቤቱ የሚገባ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

47 በቤቱም ውስጥ የሚተኛ ልብሱን ያጥባል፤ በቤቱም ውስጥ የሚበላ ልብሱን ያጥባል።

48 “ካህኑም ገብቶ ቢያይ፥ እነሆም፥ ቤቱ ከተመረገ በኋላ ደዌው በቤቱ ውስጥ ባይሰፋ፥ ደዌው ስለ ጠፋ ካህኑ ቤቱን፦ ንጹሕ ነው ይለዋል።

49 ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ይወስዳል።

50 አንደኛውንም ወፍ በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርዳል።

51 የዝግባውን እንጨት፥ ሂሶጱንም፥ ቀዩንም ግምጃ፥ በሕይወትም ያለውን ወፍ ወስዶ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውኃ ውስጥ ይነክራቸዋል፥ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይረጨዋል።

52 ቤቱንም በወፉ ደም፥ በምንጩም ውኃ፥ ሕይወትም ባለው ወፍ፥ በዝግባውም እንጨት፥ በሂሶጱም፥ በቀዩም ግምጃ ያነጻዋል።

53 በሕይወትም ያለውን ወፍ ከከተማ ወጥቶ ወደ ተንጣለለው ሜዳ እንዲበር ይለቀዋል፤ ለቤቱም ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ንጹሕ ይሆናል።”

54 “ይህ ሕግ ለሁሉም ዓይነት የለምጽ ደዌ፥ ለቈረቈርም፥

55 በልብስ ላይና በቤት ውስጥ ላለ የለምጽ ደዌ፥

56 ለእባጭም፥ ለብጉርም፥ ለቋቁቻም የሚሆን ነው።

57 እንዲሁም አንድ ነገር በሚረክስና በሚነጻ ጊዜ ለማልከት የሚያስችል ነው። ይህ የለምጽ ደዌ ሕግ ነው።”

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች