ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዮዲት INTRO1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)መግቢያ እንደ መጽሐፈ ዮዲት አቀራረብ፥ ዮዲት ሕዝቧን የሚያድን ሥራ ያከናወነችው የባቢሎን ንጉስ ናቡከደነጾር አሦርያን በሚያስተዳድርበትና ሆሎፎርነስም የጦር አዛዡ በነበረበት ወቅት ነው። ሆኖም የዚህ መጽሐፍ ዋና ትኩረት ታሪክና መልክዓ ምድር ማስተማር ሳይሆን በእግዚአብሔር ጠባቂነትና መጋቢነት መታመን ትልቅ ቦታ እንዳለው ማሳየት ነው። ከዚሁም ጋር በተያያዘ፥ ለኢየሩሳሌም የአምልኮ ማእከል ለሆነው ቤተ መቅደስ፥ እንዲሁም ለአይሁድ እምነትና ባሕል ለየት ያለ ስፍራ እንደተሰጠ በማሰብ ማንበብ ብዙ ነገሮችን ለማስተዋል ይረዳል። የዮዲት መጽሐፍ በእግዚአብሔር የተመረጠው ሕዝብ በጠላቶቹ ላይ የተቀዳጀውን ድል ይተርካል። በአንድ በኩል ዓለምን በሙሉ በናቡከደነጾር እግር ሥር ለማንበርከክ እና ሌሎች እምነቶችን ለማጥፋት ብሎም ናቡከደነጾርን እንዲያመልኩ ለማድረግ የተመኘው ታላቁ የሆሎፎርኒስ ሠራዊት አይሁድንም ማንበርከክ ሲፈልግ ይታያል። እንግዲህ በጦር መሣርያ፥ በሀብትና በሕዝብ ብዛት በፍጹም የማይመጣጠኑ ጥቂት አይሁዳውያን አደጋ ላይ ወድቀዋል። አይሁዳውያን በቤጤልዋ ተከበው የውሃ አቅርቦቱም በመቋረጡ ምክንያት እጅ ወደ መስጠት ተቃረቡ። በዚህ ጊዜ ነው፥ በእግዚአብሔር የታመነችው፥ ቆራጧና ብልኂቷ መበለት ዮዲት ብቅ ያለችው። በጀግንነቷም የፈራውን ሕዝብ እና ሠራዊት አነቃቃች። በእግዚአብሔር ላይ እምነት ያጐደሉትን የከተማዋን ሽማግሌዎች ገሠጸች፤ ከዚያም ያቀደችው ሐሳብ እንዲሳካለት ለጸሎት ተደፋች። ዮዲት ራስዋን አስጊጣ ሆሎፎርነስ በውበቷ ለመማረክ ሄደች። እርሱም በመጠጥ ራሱን ስቶ ነበርና ብቻዋን በሆነች ጊዜ አንገቱን ለመቁረጥ ቻለች። አሦራውያንም በፍርሃት ተዋጡ፤ መሸሽም ጀመሩ። አይሁዳውያኑም ሠፈራቸውን በዘበዙ። በመዝሙርም ዮዲትን ከፍ ከፍ አደረጉ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም በመሄድ ታላቅ ምስጋናን አቀረቡ። የመጽሐፈ ዮዲት አተራረክ በአንድ ወጥነት የተጎንጎነ ነው። በአንዳንድ ገጽታዎቹ ከራእያዊ ጽሑፎች ጋር ይቀራረባል። ከዚህም አኳያ የናቡከደነጾር ታማኝና ደጋፊ የሆነው ሆሎፎርኒስ የእርኩስ መንፈስ ኃይላት መገለጫ ነው። ዮዲት የስሟ ትርጒም አይሁዳዊት ማለት ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው፥ በዚያን ዘመን፥ እስራኤል በእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር በሌላ በምንም መመካት የማይችል ሕዝብና ሀገር ነበር። ዮዲት በእግዚአብሔር ተደግፋ ድልን ተጎናጸፈች ማለት፥ የአይሁድ ሕዝብ በእግዚአብሔር ብቻ በመታመን ይድናል ማለት ነው። ስለሆነም ዮዲት ለአይሁዳውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ምክንያትነት ትወክላለች። ተስፋ አስቆራጭ በሆነም ሰዓት ጭምር አምላክ በደካማዋ ሴት አማካኝነት ድል ማምጣቱ፥ በማንኛውም ከባድና ፈታኝ ወቅት የሕዝቡ ጋሻ፥ መሸሻና መመኪያ እግዚአብሔር እንደሆነ ያሳያል። የእስራኤል ሕዝብ ከድል በኋላ የሄደው ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ነበር። በመጽሐፈ ዮዲት ውስጥ የምናገኘውን ፍሬ ነገር በትንቢተ ዳንኤል ውስጥም ልናገኘው እንችላለን። ሁሉ ነገር መጥፋቱ ነው፥ ምንም ተስፋ የለም፥ በተባለበት ሰዓት እግዚአብሔር ለታማኝ አገልጋዮቹ እንደሚገለጽ ከትንቢተ ዳንኤልም መማር እንችላለን። ለእግዚአብሔር እንጂ ለናቡከደነጾር ምስል አንሰግድም ያሉት ሦስቱ የዳንኤል ወደጆች በእቶን እሳት ተጥለው እንደነበር በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ሦስት ውስጥ እናነባለን። ወደ እሳት ከመግባታቸውም በፊት ሆነ በኋላ እንደ ሰው ከተመለከትነው ማንም የሚደርስላቸው አልነበረም። ሆኖም ምንም አቅም የሌላቸው በሁሉን ቻይ አምላክ ሲታደጉ እናያለን። እንዲሁም ነቢዩ ዳንኤል (ዳንኤል ምዕራፍ ስድስት ላይ) በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ቢጣልም እንኳን ኃያል አምላክ እንዴት እንዳተረፈው ማስተዋል ይቻላል። አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት ከአሦራዊያን የሚመጣ ስጋት (1፥1—3፥10) የቤቱሊያ ከበባ (4፥1—7፥32) ዮዲት፥ የጌታ መሣሪያ (8፥1—10፥10) ዮዲት ወደ ጦር ሜዳ መውጣት (10፥11—13፥20) ድልና የምስጋና ዝማሬ (14፥1—16፥25) ምዕራፍ |