ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዮዲት 9 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ዮዲት ግን በግንባርዋ ተደፍታ በራስዋ ላይ አመድ ነሰነሰች፥ የለበሰችውንም ማቅ ገለጠች፤ በኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ቤት የማታ ዕጣን በሚቀርብበት ጊዜ፥ ዮዲት በታላቅ ድምጽ ወደ ጌታ ጮኸች፤ እንዲህም አለች፦ 2 የአባቴ የስምዖን አምላክ ጌታ ሆይ! የድንግሊቱን ማኅጸን በመፍታት ላረከሱአት፥ ጭኗን በመግለጥ ላሳፈሩአት፥ ማኅጸኗን በማርከስ ላዋረዷት፥ ይበቀል ዘንድ ለመጻተኛ ሰይፍን ሰጠህን፤ አንተ “አይሆንም” ብለህ ነበር፥ እነርሱ ግን አደረጉት። 3 ስለዚህም አለቆቻቸውን ለመገደል አሳልፈህ ሰጠህ፥ አልጋቸውም በአታላይነታቸው ኅፍረት ረከስ፥ በደም ተነከረ፥ ባሮቹን ከጌቶቻቸው ጋር፥ ጌቶችንም በዙፋኖቻቸው ላይ መታህ። 4 ሚስቶቻቸውን ለንጥቂያ፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለምርኮ አሳልፈህ ሰጠህ፥ ምርኮአቸውን ለተወደዱ ልጆች፥ ለአንተ በቅንዓት ለተቃጠሉ፥ የደማቸው መርከስ ለጠሉ፥ ከዚያም ወደ አንተ ለጮሁት ተከፋፈለ፤ አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እኔን መበለቲቱን ስማኝ። 5 ያለፈውን፥ የአሁኑንና የወደፊቱን አንተ ሠርተሀል፤ አሁን ያለውንና በኋላ የሚመጣውን አንተ ቀርጸሃል፤ አንተ ያሰብከው ሆኗል። 6 የዓቀድከው ነገር ከፊትህ ቀርበው “እነሆ መጥተናል” ይላሉ፤ መንገዶችህ ሁሉ የተዘጋጁ ናቸው፥ ፍርድህንም አስቀድሞ የታወቀ ነው። 7 እነሆ፥ የአሦር ሰዎች ከሠራዊታቸው ጋር በዝተዋልና፥ በፈረሶቻቸውና በጋላቢዎቻቸው ተመክተዋል፥ በእግረኛ ሠራዊታቸው ተኩራርተዋል፥ በጋሻቸውና በጦራቸው፥ በቀስትና በወንጭፋቸው ታምነዋል፤ ጦርነትን ሰባሪ ጌታ መሆንህን አላወቁም፤ 8 ሥምህም ጌታ ነው፤ በክንድህ ኃይላቸውን ስበር፥ በቁጣህ ጥንካሬያቸውን አድቅቅ፤ መቅደስህን ለማርከስ፥ የክቡር ስምህ ማረፊያ የሆነውን ድንኳን ለማሳደፍ፥ የመሠዊያህንም ቀንድ ለመስበር መክረዋልና። 9 ትዕቢታቸውን ተመልከት፥ ቁጣህን በላያቸው ላይ ላክ፥ የአሰብሁት እንድፈጽም ለእኔ ለመበለቲቱ ብርቱ እጅን ስጠኝ። 10 በአንደበቴ ማታለል ባርያው ከጌታው ጋር፥ ጌታውም ከአገልጋዩ ጋር ምታ፤ ትዕቢታቸውን በሴት እጅ ስበር። 11 ብርታትህ በቍጥር፥ ኃይልህም በጠንካራ ሰዎች ላይ አይደገፍምና፤ ነገር ግን የትሑታን አምላክ፥ የታናናሾች ረዳት፥ የደካሞች ድጋፍ፥ ለተገፉ መጠለያ፥ ተስፋ ለቆረጡ አዳኝ ነህ። 12 የአባቴ አምላክ፥ የእስራኤል ርስት፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ የውኆች ፈጣሪ፥ የፍጡራን ሁሉ ንጉሥ ሆይ፥ እባክህን እባክህን ጸሎቴን ስማኝ! 13 በቃል ኪዳንህ፥ በቤተ መቅደስህ፥ በጽዮን ተራራና ልጆችህ በወረሱት ቤት ላይ የጥፋት ትልሞች የነደፉትን ሁሉ የሚያታልሉ ቃላቶቼ እንዲያቆስላቸውና እንዲያጠፋቸው አድርግ። 14 ሕዝቦችህ ሁሉና ነገዶች ሁሉ፥ አምላክ አንተ ብቻ እንደሆንህ፥ ከሁሉም በላይ የኃያልና የብርታት አምላክ፥ ከአንተ በቀር እስራኤልን የሚታደግ ሌላ እንደሌለ እንዲያውቁ አድርግ። |