Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ዮዲት 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ዮዲት የዮዲት ገለጻ

1 በዚያን ጊዜ ስለዚህ ጉዳይ ዮዲት ሰማች፤ እርሷም የሜራሪ ልጅ፥ የዑኽ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ ዖዚኤል ልጅ፥ የሒልቂያ ልጅ፥ የአናንያ ልጅ፥ የጌድዮን ልጅ፥ የራፋይም ልጅ፥ የአሂቱብ ልጅ፥ የኤልያስ ልጅ፥ የሒልቅያ ልጅ፥ የኤልያብ ልጅ፥ የናትናኤል ልጅ፥ የሳላሚኤል ልጅ፥ የሳራሳዳይ ልጅ፥ የእስራኤል ልጅ ናት።

2 ከነገዷና ከወገኗ የሆነው ባሏ ምናሴ፥ በገብስ መከር ጊዜ ሞተ።

3 በእርሻ ውስጥ ነዶ ከሚያስሩ ሰዎች ቆሞ ሳለ ራሱን ንዳድ መታው፥ ታምሞ ተኛ፤ በገዛ ሀገሩ በቤቱሊያ ከተማ ሞተ፤ በዶታንና በባላሞን መካከል በሚገኝ እርሻ ውስጥ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት።

4 ዮዲትም መበለት ሆና ሦስት ዓመት ከአራት ወር በቤትዋ ተቀመጠች።

5 በቤትዋ ጣራ ላይ ለራስዋ ድንኳን ሠራች፥ በወገቧ ማቅ ታጠቀች፥ የመበለትነት ልብስዋንም ለበሰች።

6 በሰንበት ዋዜማና በሰንበት፥ በመባቻ ዋዜማና በመባቻ፥ በእስራኤል ቤት በዓላትና የደስታ ቀኖች ካልሆነ በቀር በመበለትነትዋ ጊዜ ሁሉ ትጾም ነበር።

7 መልከ መልካምና መልኳም እጅግ የሚያምር ነበረች፤ ባሏ ምናሴም ወርቅና ብር፥ ወንዶች አገልጋዮችና ሴቶች አገልጋዮች፥ ከብቶችንና እርሻዎችን ትቶላት ነበር፤ በእርሱም ትኖር ነበር።

8 ፈጽማ እግዚአብሔርን ስለምትፈራ፥ ስለ እርሷ ክፉ የሚናገረ ማንም ሰው አልነበረም።


ዮዲትና አዛውንቶቹ

9 ዮዲት ሕዝቡ ውኃ በማጣታቸው ተስፋ ቆርጠው በገዢያቸው ላይ የተናገሩትን ክፉ ነገር፥ እንዲሁም ዑዚያ ከአምስት ቀን በኋላ ከተማይቱን ለአሦራውያን አሳልፎ እንደሚሰጥ ለሕዝቡ በመሐላ የተናገራቸውን ሁሉ በሰማች ጊዜ፥

10 የንብረቷ ሁሉ አስተዳዳሪ የነበረችውን ሴት፥ ዑዚያንን፥ ካብሪስንና ካርሚስን፥ የከተማዋን ሽማግሌዎች እንድትጠራላት ወደ እነርሱ ላከቻት።

11 እነርሱም ወደ እርሷ መጡ፥ እርሷም እንዲህ አለቻቸው፦ “የቤቱሊያ ነዋሪዎች ገዢዎች ሆይ ስሙኝ! በዚህ ቀን በሕዝቡ ፊት የተናገራችሁት ንግግር ልክ አይደለም፤ በእግዚብአብሔርና በእናንተ መካከልም ይህን መሐላ አቆማችሁ፥ ጌታ ባይረዳችሁ ከተማይቱን ለጠላቶቻችን አሳልፋችሁ እንደምትሰጡ ተናገራችሁ።

12 ዛሬ እግዚአብሔርን የምትፈታተኑና በሰዎች መካከል እንደ እግዚአብሔር ሆናችሁ የምትቆሙ እነማናችሁ?

13 ሁሉ ቻይ ጌታን እየመረመራችሁት ነው፥ ነገር ግን እስከ ዘለዓለም ምንም አታውቁም።

14 የሰው ልብ ጥልቀት ማግኘት አትችሉም፥ በአእምሮው የሚያስበውንም መያዝ አትችሉም፥ ይህን ሁሉ የሠራውን እግዚአብሔርን እንዴት ትመረምራላችሁ? ሐሳቡን ማወቅ ወይም ማስተዋል እንዴት ይሆንላችኋል? ወንድሞቼ ሆይ አይሆንም፥ ጌታ አምላካችንን አታስቆጡት።

15 በአምስቱ ቀን ውስጥ ሊረዳን ባይፈልግ እንኳ በፈለገ ጊዜ ሊያድነን ወይም በጠላቶቻችን ፊት ሊያጠፋን ሥልጣን አለው።

16 በጌታ አምላካችን ሐሳብ ላይ የማረጋገጫ ዋስትና አታድርጉ፥ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንደ ሰው የሚያስፈራሩትና እንደ ሰው ልጅ በመደለያ የሚታለል አይደለም።

17 ስለዚህ ማዳኑን በመጠባበቅ ሳለን እንዲረዳን እንጥራው፥ የሚያስደስተው ከሆነ ድምጻችንን ይሰማል።”

18 በቀድሞ ዘመን እንደ ተደረገ በትውልዳችን ወይም በእነዚህ ቀኖች፥ ነገድ ወይም ጐሣ ወይም ሕዝብ ወይም ከተማ፥ ከእኛ መካከል በእጅ የተሠሩ አማልክትን ሊያመልክ የተነሣ የለም።

19 አባቶቻችን ይህን በማድረጋቸው ነው ለሰይፍና ለብዝበዛ የተሰጡት፥ በጠላቶቻችንም ፊት ብዙ በድን ወደቀ።

20 እኛ ግን ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ አናውቅም፥ ስለዚህ እኛን ወይም ወገኖቻችንን እንደማይንቀን ተስፋ እናደርጋለን።

21 እኛ ከተያዝን ይሁዳ በሙሉ ትያዛለች፥ መቅደሳችን ቦታችንም ይዘረፋል፥ በመርከሱም ደማችንን ይፈልገዋል።

22 የወንድሞቻችን መገደልና የምድሪቱ መያዝ፥ የርስታችንም መጥፋት ባርያዎች በምንሆንበት ሁሉ በአሕዛብ መካከል በራሳችን ላይ ይመለሳል፤ በሚገዙን ፊትም እንቅፋትና ስድብ እንሆናለን።

23 ባርነታችን ሞገስን አይሰጠንም፥ ነገር ግን ጌታ አምላካችን ወደ ውርደት ይለውጠዋል።

24 ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ፥ ለወንድሞቻችን ምሳሌ እናሳያቸው፥ ሕይወታቸው በእኛ ተደግፏልና፥ የቤተ መቅደሱና የመሠዊያው ኃላፊነት በእኛ ላይ አርፏልና።

25 በተጨማሪም አባቶቻችንን እንደ ፈተነ እኛንም ለፈተነን ለጌታ አምላካችን ምስጋና እናቅርብ።

26 አብርሃም ላይ ያደረገውንና ይስሐቅን እንዴት እንደ ፈተነው፥ በያዕቆብም ላይ በሶርያ መስጴጦምያ የእናቱን ወንድም የላባን በጎች በሚጠብቅበት ጊዜ ምን እንደ ደረሰበት አስታወሱ።

27 ልባቸውን ለመመርመር እንዳደረገው እኛን በእሳት አልፈተነንም፥ ወይም አልተበቀለንም፤ እግዚአብሔር ወደ እርሱ የሚቀርቡትን ሊገሥጻቸው ይቀጣቸዋልና።

28 ዑዚያ እንዲህ አላት፦ “የተናገርሽውን ሁሉ በጥሩ ልብ ተናገርሽ፥ ቃልሽንም የሚቃወም ማንም የለም።

29 ጥበብሽ የተገለጠው ዛሬ ብቻ አይደለም፥ ከድሮ ጀምሮ ከሕይወትሽ መጀመሪያ ጀምሮ አስተዋይነትሽን በሕዝቡ ሁሉ አወቀው፥ የልብሽ ተፈጥሮ ቅን ነውና።

30 ነገር ግን በጣም የተጠማው ሕዝብ ቃል የገባነውን እንድንፈፅም አስገደዱን፥ የማንተላለፈውን መሐላ አመጡብን።

31 አሁንም አንቺ እግዚአብሔርን የምትፈሪ ሴት ነሽና ጌታ ዝናብ እንዲልክና ጉድጓዳችንን ሁሉ እንዲሞላ ጸልይልን፤ ከዚያ ወዲህም አንዝልም።”

32 ዮዲትም እንዲህ አለቻቸው፦ “ስሙኝ፥ በወገኖቻችን ዘንድ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ አንድ ነገር አደርጋለሁ፤

33 በዚች ሌሊት እናንተ በበሩ ቁሙ፥ እኔም ከአገልጋዬ ጋር እወጣለሁ፤ ከተማይቱን ለጠላቶቻችን አሳልፈን እንሰጣለን ባላችሁባቸው ቀኖች ጌታ በእጄ እስራኤልን ያድናል።

34 እናንተ ግን የምሠራውን ለማወቅ አትሞክሩ፥ የምሠራውን እስክፈጽም ድረስ አልነግራችሁምና።”

35 ዑዚያና ገዢዎቹም፥ “በሰላም ሂጂ፥ ጌታ እግዚአብሔር ጠላቶቻችንን ለመቀበል በፊትሽ ይሁን” አሏት።

36 ከዚህ በኋላ ከድንኳኑ ወጥተው ወደየሥራቸው ሄዱ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች