Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ዮዲት 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የአኪዮር ለእስራኤሎች ተላልፎ መስጠት

1 ሸንጎውን ከበው የነበሩት ሰዎች ጫጫታቸውን አቋርጠው ዝም ባሉ ጊዜ የአሦር ዋና የጦር አዛዥ ሆሎፎርኒስ በእንግዳ ሕዝቦች እና በሞዓብ ልጆች ሁሉ ፊት አኪዮርን እንዲህ አለው፦

2 አንተ አኪዮር፥ እናንተም የኤፍሬም ቅጥረኞች፥ አምላካቸው ስለሚጠብቃቸው ከእስራኤል ልጆች ጋር አትዋጉ ብላችሁ ዛሬ ትንቢት የምትናገሩን እናንተ ማን ናችሁ? ከናቡከደነፆር በቀር ሌላ አምላክ ማን ነው? እርሱ የጦር ኃይሉን ልኮ ከምድረ ገጽ ያጠፋቸዋል፤ አምላካቸው አያድናቸውም፤

3 እኛ የናቡከደነፆር ባርያዎች እንደ አንድ ሰው እንመታቸዋለን፤ የፈረሰኞቻችንንም ኃይል ሊቋቋሙ አይችሉም።

4 እናቃጥላቸዋለን፤ ተራሮቻቸው በደማቸው ይሰክራሉ፥ ሜዳዎቻቸው በአስክሬን ይሞላሉ፤ የእግራቸው ፍለጋ እንኳ ሊቋቋመን አይችልም፤ ፈጽመው ይጠፋሉ፥ የምድር ሁሉ ጌታ የሆነው ናቡከደነፆር ብሏልና፤ እርሱ ተናግሮአልና፤ ንግግሩ በከንቱ አይቀርም።

5 አንተም አክዮር አሞናዊ ቅጥረኛ ከዳተኛ ሆነህ ነው ይህን የተናገርኸው፤ ከዛሬ ጀምሮ ከግብጽ የወጣውን ዘር እስክበቀለው ድረስ ፊቴን አታየውም።

6 ተመልሼ ስመጣ የወታደሮቼና የአገልጋዮቼ ጦር ጐኖችህን ይወጋል፤ ከቁስለኞቻቸው መሃል ትወድቃለህ፤

7 አሁን ባርያዎቼ ወደ ተራራማው አገር ይወስዱሃል፥ እዚያም በአንድ ከተማ መተላለፊያ ይጥሉሃል።

8 ከእነርሱ ጋር እስክትጠፋ ድረስ አትሞትም።

9 አልያዝም ብለህ በልብህ ካሰብህ ፊትህ አይውደቅ፤ እኔ ተናግሬአለሁ፥ ከቃሌም የሚወድቅ የለም።

10 ከዚህ በኋላ ሆሎፎርኒስ በድንኳኑ ውስጥ ቆመው ለነበሩት ባርያዎቹ አክዮርን ይዘው ወደ ቤቱሊያ እንዲወስዱትና ለእስራኤልም ልጆች አሳልፈው እንዲሰጡት አዘዘቸው።

11 ባርያዎቹም ያዙትና ከሰፈሩ ውጭ ወደ ሜዳ ወሰዱት፤ ከሜዳው ወደ ተራራማው አገር ወጡና ከቤቱሊያ በታች ወዳሉት ምንጮች ደረሱ፤

12 የከተማዋ ሰዎች ባዩአቸው ጊዜ መሣሪያቸውን ይዘው ከከተማዋ ወጥተው ወደ ተራራው ጫፍ ወጡ፥ ወንጭፍ የያዙ ሰዎች ድንጋይ እየወረወሩ ወደ ላይ እዳይወጡ ከለከሉአቸው።

13 በተራራው ተደብቀው አክዮርን አስረው በተራራው ሥር ጥለውት ወደ ጌታቸው ተመለሱ።

14 የእስራኤልም ልጆች ግን ከከተማቸው ወረዱና ወደ እርሱ ሄዱ፤ ፈትተውትም ወደ ቤቱሊያ አመጡት፥ በከተማቸው ገዢዎች ፊት አቀረቡት፤

15 በዚያን ዘመን ገዢዎች የነበሩት ከስምዖን ነገድ የሆነ የሚካ ልጅ ዑዚያ፥ የጐቶኒኤል ልጅ ካብሪስና የመልኪኤል ልጅ ካርሚስ ናቸው።

16 የከተማይቱን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠሩ፥ ወጣቶቻቸውና ሴቶቻቸው ሁሉ ወደ ጉባኤው መጡ፤ አክዮርን በሕዝቡ መካከል አቆሙና ዑዚያ ስለተደረገው ነገር ጠየቀው።

17 አክዮር በሆሎፎርኒስ ጉባኤ ላይ የተባለውን፥ በአሦር ታላላቅ ሰዎች ፊት የተናገረውን ሁሉና ሆሎፎርኒስ በእስራኤለ ቤት ላይ የፎከረውን ሁሉ ነገራቸው።

18 በዚህ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ወድቀው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፥ እንዲህም ሲሉ ጮኹ፦

19 “የሰማይ አምላክ ጌታ ሆይ፥ ትዕቢታቸውን ተመልከት፥ የወገኖቻችንን ውርደት አይተህ ይቅር በል፤ በዚህች ቀን ለአንተ የተቀደሱትን ፊት ተመልከት።”

20 ከዚህ በኋላ አክዮርን አጽናኑት፥ እጅግም አከበሩት።

21 ዑዚያ ከጉባኤው ወደ ቤቱ ወሰደውና ለሽማግሌዎች ግብዣ አደረገ፤ በዚያች ሌሊት ሙሉ የእስራኤል አምላክ እንዲረዳቸው ጠሩት።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች