Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ዮዲት 5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የሆሎፎርኒስና የሹማምንቱ ጉባኤ

1 የእስራኤል ልጆች ለጦርነት መዘጋጀታቸው፥ ወደ ተራራማው ከተማ የሚያስተላልፈውን መንገድ መዝጋታቸው፥ የከፍተኛ ኮረብታዎቻቸውን ራሶች ማጠራቸው፥ በሜዳዎቻቸው ወጥመድ ማበጀታቸው ለአሦር ዋና የጦር አዛዥ ለሆሎፎርኒስ ተነገረው፤

2 እርሱም እጅግ በጣም ተቆጥቶ የሞዓብን ገዢዎች፥ የአሞንን የጦር አዛዦችና የባሕር ጠረፍ ገዢዎችን ጠራ፤

3 እንዲህም አላቸው፦ “የከነዓን ልጆች እስቲ ንገሩኝ፥ በተራራማው አገር የሚቀመጠው ሕዝብ ምን ዓይነት ነው? በየትኞቹ ከተሞችስ ይኖራሉ? የሠራዊታቸው ብዛት ምን ያህል ነው? ኃይላቸውና ጽናታቸውስ ምን ላይ ነው? ሠራዊታቸውን የሚመራና እንደ ንጉሣቸው የተሾመስ ማን ነው?

4 በምዕራብ ከሚኖሩ ሰዎች ሁሉ እነርሱ ሊቀበሉኝ ያልመጡት ስለምንድን ነው?”

5 የአሞን ልጆች ሁሉ መሪ የሆነው አክዮር እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እንግዲህ ጌታዬ ከባርያህ አንደበት ቃል ስማ፤ በዚህ በተራራማው አገር፥ በአጠገብህ ስለሚኖሩ ሕዝብ እውነቱን እነግርሃለሁ፤ ከባርያህ አንደበት ሐሰት አይወጣም።

6 ይህ ሕዝብ የከለዳውያን ዘር ነው።

7 በፊት በእንግድነት በመስጴጦምያ ይኖሩ ነበር፥ ምክንያቱም በከላውዴዎን የነበሩት የአባቶቻቸውን አማልክት አንከተልም ብለው ነበርና።

8 የአባቶቻቸውን መንገድ ትተዋልና፥ አሁን ያወቁትን የሰማዩን አምላክ አምልከዋልና፥ ከአማልክቶቻቸው ፊት አባረሩአቸው፤ ወደ መስጴጦምያ ሸሸተው መጡ፥ በዚያም ብዙ ዘመን ኖሩ።

9 አምላካቸው ከሚኖሩበት አገር ወጥተው ወደ ከነዓን ምድር እንዲሄዱ አዘዛቸው፤ እዚያም ሄደው ሲቀመጡ በዚያ በብዙ ወርቅ፥ በብዙ ብርና በብዙ መንጋዎች በለጸጉ።

10 የከነዓንን ምድር ረሃብ ባጠቃት ጊዜ ወደ ግብጽ ወረዱ፥ እራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ በዚያ ተቀመጡ፤ በዚያም በጣም ተባዙ፥ ዘራቸውም ከቍጥር በላይ ሆነ።

11 ነገር ግን የግብጽ ንጉሥ በእነርሱ ላይ ተነሣባቸው፥ በጡብ ሥራ ላይ በማሰማራት አላግባብ ተጠቀመባቸው፤ ጨቆናቸው፥ ባርያዎችም አደረጋቸው።

12 ወደ አምላካቸው ጮኹ፥ እርሱም በማይድን መቅሠፍት የግብጽን ምድር በሙሉ መታ፤ ግብጻውያንም ከፊታቸው አስወጡአቸው።

13 እግዚአብሔርም በፊታቸው ቀይ ባሕርን አደረቀላቸው፤

14 በሲናና በቃዴስ በርኔ መንገድ መራቸው፤ በምድረ በዳ የሚኖሩትንም ሁሉ አባረሩአቻው።

15 በአሞራውያን ምድርም ተቀመጡ፤ ሐሴቦናውያንንም ሁሉ በኃይላቸው አጠፉአቸው፤ ዮርዳኖስን ተሻግረው ተራራማውን አገር ሁሉ ወረሱ።

16 ከነዓናውያንን፥ ፌርዛውያንን፥ ኢያቡሳውያንን፥ ሴኬማውያንንና ጌርጌሳውያንን ሁሉ ከፊታቸው አስወጥተው በዚያ ብዙ ዘመን ኖሩ።

17 በአምላካቸው ፊት ኃጢአትን እስካልሰሩ ድረስ በለጸጉ፥ ኃጢአትን የሚጠላ አምላካቸው ከእነርሱ ጋር ነውና።

18 ነገር ግን እርሱ ከወሰነላቸው መንገድ ፈቀቅ ባሉ ጊዜ በብዙ ጦርነቶች ተደመሰሱ፥ ተማርከው ወደ ባእድ አገር ተወሰዱ፤ የአምላካቸው ቤተ መቅደስ ፈረሰ፤ ከተሞቻቸውም በጠላቶቻቸው ተያዙ።

19 አሁን ግን ወደ አምላካቸው ተመልሰዋል፥ ከተበታተኑበትም ቦታ ተመልሰዋል፥ ቤተ መቅደሳቸው ያለበትን ኢየሩሳሌምንም ይዘዋል፤ ባዶውን ስለ ነበር ተራራማውን አገር ያዙ።

20 ስለዚህ አሁን አልቃዬና ጌታዬ በዚህ ሕዝብ ጥፋት ካለበት፥ በአምላካቸው ላይ ኃጢአት ከሠሩና እኛም ጥፋታቸውን ካረጋገጥን ወጥተን እንገጥማቸዋለን።

21 ያልበደሉ ሕዝቦች ከሆኑ ግን ጌታዬ አልፎአቸው ይሂድ፤ ጌታቸውና አምላካቸው ይቆምላቸዋልና፤ እኛም በምድር ሁሉ ፊት እንዋረዳለንና።

22 አኪዮር ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ በድንኳኑ ዙሪያ ከቦ የነበረ ሕዝብ ሁሉ አጉረመረመ፤ የሆሎፎርኒስ ሹማምንትና በባሕሩ ዳርና በሞዓብ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ፥ መቆራረጥ አለበት አሉ።

23 የእስራኤልን ልጆች አንፈራቸውም፤ ብርቱ ሰልፍ ለመቋቋም ኃይልና ብርታት የላቸውምና።

24 ስለዚህ አሁን ጌታ ሆሎፎርኒስ እንውጣ፤ ለሠራዊትህ ሁሉ መብል ይሆናሉ።”

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች