ዮሐንስ 18 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ እንደሰጠ ( ማቴ. 26፥47-56 ፤ ማር. 14፥43-50 ፤ ሉቃ. 22፥47-53 ) 1 ኢየሱስም ይህን ብሎ አትክልት ወዳለበት ስፍራ ወደ ቄድሮን ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ እርሱም ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ገቡ። 2 ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ብዙ ጊዜ ወደዚያ ስለ ተሰበሰቡ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ስፍራውን ያውቅ ነበር። 3 ስለዚህ ይሁዳ ወታደሮችን፥ እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና፥ በጦር መሣርያም ታጅቦ ወደዚያ መጣ። 4 ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 5 “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት። እርሱም “እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። 6 ኢየሱስም “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመሬት ላይ ወደቁ። 7 ዳግመኛ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። 8 ኢየሱስ መልሶ “እኔ ነኝ፤ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ከሆነ የምትፈልጉት እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አለ፤ 9 ይህም “ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን እንኳን አላጠፋሁም” ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። 10 ስምዖን ጴጥሮስም ሰይፍ ይዞ ስለ ነበር መዘዘውና የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም ማልኮስ ነበረ። 11 ኢየሱስም ጴጥሮስን “ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተተው፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ ላልጠጣ ነውን?” አለው። የኢየሱስ ወደ ሊቀ ካህናቱ መወሰድ ( ማቴ. 26፥57-58 ፤ ማር. 14፥53-54 ፤ ሉቃ. 22፥54 ) 12 እንግዲህ ወታደሮቹና አዛዣቸው፥ የአይሁድም ሎሌዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት፤ 13 አስቀድመውም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና። 14 ቀያፋም “ስለ ሕዝቡ ሲባል አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል” ሲል አይሁድን የመከራቸው ነበረ። ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደ ካደ ( ማቴ. 26፥69-70 ፤ ማር. 14፥66-68 ፤ ሉቃ. 22፥55-57 ) 15 ስምዖን ጴጥሮስና ሌላው ደቀመዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀመዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤ 16 ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ ቆሞ ነበር። በሊቀ ካህናቱም ዘንድ የታወቀው ሌላው ደቀመዝሙር ወጣ፤ ለበረኛይቱም ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። 17 በር ጠባቂ አገልጋይቱም ጴጥሮስን “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ አይደለህምን?” አለችው። እርሱ “አይደለሁም” አለ። 18 ይበርድ ነበረና አገልጋዮችና ሎሌዎች የከሰል እሳት አንድደው ቆመው ይሞቁ ነበር፤ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። ከሊቀ ካህናቱ ለኢየሱስ የቀረበ ጥያቄ ( ማቴ. 26፥59-66 ፤ ማር. 14፥55-64 ፤ ሉቃ. 22፥66-71 ) 19 ሊቀ ካህናቱም ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። 20 ኢየሱስም መልሶ “እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ ሁልጊዜ አስተማርሁ፤ በስውርም ምንም አልተናገርሁም። 21 ስለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? ስናገር የሰሙኝን ጠይቅ፤ እነሆ፥ እነርሱ እኔ የተናገርሁትን ያውቃሉ፤” አለው። 22 ይህንን ባለ ጊዜ በዚያ ቆመው ከነበሩት ሎሌዎች አንዱ “ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን?” ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። 23 ኢየሱስም መልሶ “ክፉ ተናግሬ እንደሆነ ስለ ክፉ መስክርብኝ፤ መልካም ተናግሬ እንደሆን ግን ስለምን ትመታኛለህ?” አለው። 24 ሐናም እንደታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው። ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደገና መካዱ ( ማቴ. 26፥71-75 ፤ ማር. 14፥69-72 ፤ ሉቃ. 22፥58-62 ) 25 ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። “አንተስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አይደለህምን?” አሉት። እርሱም “አይደለሁም፤” ብሎ ካደ። 26 ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮች መካከል አንዱ፥ ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመድ፥ “በአትክልቱ ስፍራ ከእርሱ ጋር አይቼህ አልነበረምን?” አለው። 27 ጴጥሮስም በድጋሚ ካደ፤ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት እንደ ቆመ ( ማቴ. 27፥1-2 ፤ 11-14 ፤ ማር. 15፥1-5 ፤ ሉቃ. 23፥1-5 ) 28 ኢየሱስንም ከቀያፋ ወደ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ ማለዳም ነበረ፤ እነርሱም እንዳይረክሱ፥ ይልቁንም የፋሲካን በግ እንዲበሉ በማለት ወደ ገዢው ግቢ አልገቡም። 29 ስለዚህም ጲላጦስ ወደ ውጭ፥ ወደ እነርሱ ወጥቶ “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ምን ዓይነት ክስ ነው አላቸው?” አላቸው። 30 እነርሱም መልሰው “ይህ ሰው ክፉ አድራጊ ባይሆን ለአንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር” አሉት። 31 ጲላጦስም “እናንተ ወስዳችሁ በሕጋችሁ ፍረዱበት” አላቸው። አይሁድም “እኛስ ማንንም ለመግደል አልተፈቀደልንም፤” አሉት፤ 32 ይህም ኢየሱስ በምን ዓይነት ሞት እንደሚሞት ሲያመለክት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነብር። 33 ጲላጦስም እንደገና ወደ ገዢው ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” አለው። 34 ኢየሱስም መልሶ “አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን? ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህ?” አለው። 35 ጲላጦስ መልሶ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል?” አለው። 36 ኢየሱስም መልሶ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴ ከዚህ ዓለም ብትሆን ኖሮ፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ ነገር ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” አለው። 37 ጲላጦስም “እንግዲያውስ ንጉሥ ነህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ ንጉሥ እንደሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ተወልጃለሁ፤ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” አለው። 38 ጲላጦስ “እውነት ምንድነው?” አለው። ይህንንም ብሎ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጣና “እኔስ አንዲት በደል እንኳን አላገኘሁበትም። 39 ነገር ግን በፋሲካ አንድ ሰው እንድፈታላችሁ ልማድ ሆኖአል፤ የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” አላቸው። 40 ሁሉም በድጋሚ “በርባንን እንጂ ይህን ሰው አይደለም” እያሉ ጮኹ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ። |