Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ኢዮብ 12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦

2 “በእርግጥም እናንተ የሕዝብ ድምፅ ናችኋ! ጥበብም ከእናንተ ጋር ትሞታለቻ!

3 ነገር ግን እኔም እንደ እናንተ ማስተዋል እችላለሁ፥ ከእናንተም አላንስም፥ እንደዚህ ያለውን ነገር የማያውቅ ማን ነው?

4 ለባልንጀራው መሳለቂያ እንደሚሆን ሰው ሆኛለሁ፥ እግዚአብሔርን የጠራሁ እኔ፥ እርሱም የመለሰልኝ፥ ጻድቅና ፍጹም ሰው መሳለቂያ ሆኖአል።

5 ተደላድሎ የተቀመጠ ሰው መከራን ይንቃል፥ እግሩን ያዳለጠውንም ለመገፍተር ተዘጋጅቶአል።

6 የቀማኞች ድንኳን በደኅንነት ይኖራል፥ እግዚአብሔርንም የሚያስቈጡ ተዝናንተው ተቀምጠዋል፥ እግዚአብሔር ሁሉን በእጃቸው አምጥቶላቸዋል።”

7 “አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፥ ያስተምሩህማል፥ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።

8 ወይም ለምድር ተናገር፥ እርሷም ታስተምርሃለች፥ የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል።

9 የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?

10 የሕያዋን ሁሉ ነፍስ የሰውም ሁሉ እስትንፋስ በእጁ ናት።

11 ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ፥ ጆሮም የቃላትን እውነት ይለይ የለምን?

12 ጥበብ በሽምግልና፥ ማስተዋል በረጅም ዕድሜ ይገኛሉ።”

13 “በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ፥ በእርሱ ዘንድ ምክርና ማስተዋል አለ።

14 እነሆ፥ ካፈረሰ፥ የፈረሰው ተመልሶ አይሠራም፥ በሰውም ላይ ከዘጋ፥ ሊከፈት አይችልም።

15 እነሆ፥ ውኆቹን ቢከለክል፥ እነርሱ ይደርቃሉ። እንደገና ቢለቃቸው፥ ምድሪቱን ያጥለቀልቃሉ።

16 ኃይልና ጥበብ በእርሱ ዘንድ ናቸው፥ የሚስተውና የሚያስተው የእርሱ ናቸው።

17 አማካሪዎችንም እራቁታቸውን ይሰዳቸዋል፥ ፈራጆችንም ሞኝ ያደርጋል።

18 የነገሥታትንም እስራት ይፈታል፥ ወገባቸውንም በመታጠቂያ ያስራቸዋል።

19 ካህናትን እንደ ምርኮኛ ይወስዳቸዋል፥ ኃያላንንም ይገለብጣቸዋል።

20 ከታመኑ ሰዎችም ቋንቋን ያርቃል፥ የሽማግሌዎችንም ማስተዋል ይወስድባቸዋል።

21 በአለቆች ላይ ንቀትን ያፈስሳል፥ የብርቱዎችንም መታጠቂያ ያላላል።

22 ከጨለማ ውስጥ ጥልቅን ነገር ይገልጣል፥ የሞትንም ጥላ ወደ ብርሃን ይለውጣል።”

23 አሕዛብን ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ እነርሱንም ያጠፋል፥ አሕዛብንም ያሰፋል፥ እነርሱንም ያፈልሳቸዋል።

24 ከምድር አሕዛብ አለቆች ዘንድ ማስተዋልን ያስወግዳል፥ መንገድም በሌለበት በረሃ ያቅበዘብዛቸዋል።

25 ብርሃንም በሌለበት ጨለማ ይርመሰመሳሉ፥ እንደ ሰካራም ያቅበዘብዛቸዋል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች