ኤርምያስ 45 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ለባሮክ የተደረገ የመጽናኛ ቃል 1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት የኔርያ ልጅ ባሮክ ኤርምያስ በቃል እየነገረው እነዚህን ቃሎች በመጽሐፍ በጻፋቸው ጊዜ፥ ነቢዩ ኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 2 “ባሮክ ሆይ! የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይልሃል፦ 3 አንተ፦ ‘ጌታ በሕመሜ ላይ ኀዘንን ጨምሮብኛልና ወዮልኝ! በልቅሶዬ ጩኸት ደክሜአለሁ፥ ዕረፍትንም አላገኘሁም’ ብለሃል። 4 እንዲህ በለው፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የሠራሁትን አፈርሳለሁ፥ የተከልሁትንም እነቅላለሁ፤ ይኸውም ምድሪቱን በሞላ ነው። 5 አንተም ለራስህ ታላቅን ነገር ትሻለህን? አትሻ፥ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ፥ እነሆ፥ ክፉ ነገርን አመጣለሁና፥ ይላል ጌታ፤ ነገር ግን በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ።” |