Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ኤርምያስ 39 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ኢየሩሳሌም በጠላት እጅ መውደቋ

1 በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በዘጠነኛው ዓመት፥ በአሥረኛው ወር፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤

2 በሴዴቅያስም በዓሥራ አንደኛው ዓመት፥ በአራተኛው ወር፥ ከወሩም በዘጠነኛው ቀን የከተማይቱ ቅጥር ተጣሰ።

3 ኢየሩሳሌምም በተያዘች ጊዜ የባቢሎንም ንጉሥ አለቆች ሁሉ፥ ኤርጌል ሳራስር፥ ሳምጋር ናቦ፥ የራፌሱ ሠርሰኪም፥ የራብማጉ ኤርጌል ሳራስር፥ ከተረፉት ከባቢሎን ንጉሥ አለቆች ሁሉ ጋር ገብተው በመካከለኛው በር ውስጥ ተቀመጡ።

4 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ወታደሮቹም ሁሉ ባዩአቸው ጊዜ ኰበለሉ፥ በሌሊትም በንጉሡ አትክልት መንገድ በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በነበረው በር በኩል ከከተማይቱ ወጡ፤ መንገዳቸውንም ወደ ዓረባ አድርገው ተጓዙ።

5 የከለዳውያንም ሠራዊት ተከታተላቸው፥ በኢያሪኮም ሜዳ ሴዴቅያስን ደረሱበት፤ እርሱንም ይዘው በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ሪብላ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር አመጡት፤ እርሱም ፍርድን በእርሱ ላይ ተናገረ።

6 የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ልጆች ዓይኑ እያየ በሪብላ ገደላቸው፤ የባቢሎንም ንጉሥ የይሁዳን መሳፍንት ሁሉ ገደለ።

7 የሴዴቅያስንም ዐይን አወጣ፥ ወደ ባቢሎንም ለመውሰድ በሰንሰለት አሰረው።

8 ከለዳውያንም የንጉሡንና የሕዝቡን ቤቶች በእሳት አቃጠሉ፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ።

9 የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን በከተማይቱ የቀሩትን ሕዝብ፥ ወደ እርሱም ኮብልለው የነበሩትን ሰዎች፥ የቀረውንም የሕዝቡን ቅሬታ ወደ ባቢሎን ማርኮ አፈለሳቸው።

10 የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ምንም የሌላቸውን አንዳንድ ድሆች በይሁዳ አገር ተዋቸው፥ በዚያው ጊዜም የወይኑን ቦታዎችና እርሻዎችን ሰጣቸው።


ነቢዩ ኤርምያስ ያታደገውን አቤሜሌክን ማስታወሱ

11 የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ ኤርምያስ በዘበኞቹ አለቃ በናቡዘረዳን በኩል እንዲህ ሲል ትእዛዝን ሰጠ፦

12 “ውሰደው፥ በበጎ ተመልከተው፥ የሚሻውንም ነገር አድርግለት እንጂ ምንም ዓይነት ክፉ ነገር አታድርግበት።”

13 የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን፥ የራፋስቂሱ ናቡሽዝባንም የራብማጉ ኤርጌል ሳራስርም የባቢሎንም ንጉሥ ዋና ዋና አለቆች ሁሉ

14 ልከው ኤርምያስን ከእስር ቤት አደባባይ አወጡት፤ ወደ ቤቱም እንዲወስደው ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ ሰጡት፤ እርሱም በሕዝብ መካከል ተቀመጠ።

15 በእስር ቤትም አደባባይ ታስሮ ሳለ የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ፦

16 “ሂድ፥ ለኢትዮጵያዊውም ለአቤሜሌክ እንዲህ በለው፦ ‘የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ለበጎነት ሳይሆን ለክፋት ቃሎቼን በዚህች ከተማ ላይ አመጣለሁ፤ በዚያም ቀን በፊትህ ይፈጸማል።

17 በዚያ ቀን አድንሃለሁ፥ ይላል ጌታ፤ በምትፈራቸውም ሰዎች እጅ ተላልፈህ አትሰጥም።

18 ፈጽሜ አድንሃለሁ፥ ነፍስህም ለአንተ በምርኮ ትድናለች እንጂ በሰይፍ አንተ አትወድቅም፥ በእኔ ታምነሃልና፥ ይላል ጌታ።’ ”

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች