ኤርምያስ 24 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)መልካምና ክፉ በለስ 1 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን፥ የይሁዳንም አለቆች ጠራቢዎችንና ብረት ሠራተኞችን ከኢየሩሳሌም ማርኮ ወደ ባቢሎን ካፈለሳቸው በኋላ፥ ጌታ አሳየኝ፥ እነሆም፥ በጌታ መቅደስ ፊት ሁለት ቅርጫት በለስ ተቀምጠው ነበር። 2 በአንደኛው ቅርጫት አስቀድሞ እንደ ደረሰ በለስ የሚመስል እጅግ መልካም በለስ ነበረበት፤ በሁለተኛውም ቅርጫት ከክፋቱ የተነሣ ሊበላ የማይችል እጅግ ክፉ በለስ ነበረበት። 3 ጌታም፦ “ኤርምያስ ሆይ! የምታየው ምንድነው?” አለኝ። እኔም፦ “በለስን አያለሁ፤ እጅግ መልካም የሆነ መልካም በለስ፥ ከክፋቱም የተነሣ ሊበላ የማይችል እጅግ ክፉ የሆነ ክፉ በለስ ነው” አልሁ። 4 የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 5 “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፥ እንዲሁ ከዚህ ስፍራ ወደ ከለዳውያን ምድር የላክሁትን የይሁዳን ምርኮ በበጐነት እመለከተዋለሁ። 6 ዓይኔንም ለበጐነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፥ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም። 7 እኔም ጌታ እንደሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹምም ልባቸው ወደ እኔ ይመለሳሉና፥ ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 8 “ነገር ግን ጌታ እንዲህ ይላል፦ ከክፋቱ የተነሣ ሊበላ እንደማይችል እንደ ክፉው በለስ፥ እንዲሁ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን አለቆቹንም፥ በዚህችም አገር የሚቀሩትን የኢየሩሳሌምን ትሩፍ፥ በግብጽም አገር የሚቀመጡትን ክፉውን አደርግባቸዋለሁ። 9 በማሳድዳቸውም ስፍራ ሁሉ ለስድብና ለምሳሌ ለማላገጫና ለእርግማን ይሆናሉ፤ በምድርም መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለድንጋጤና ለክፉ ነገር አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። 10 ለእነርሱና ለአባቶቻቸውም ከሰጠኋቸው ምድር እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም እልክባቸዋለሁ።” |