ኤርምያስ 20 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ጳስኮር ነቢዩ ኤርምያስን ማሳደዱ 1 በጌታም ቤት የተሾመው አለቃ፥ የኢሜር ልጅ ካህኑ ጳስኮር ኤርምያስ በዚህ ነገር ትንቢት ሲናገር ሰማ። 2 ጳስኮርም ነቢዩን ኤርምያስን መታው፥ በጌታም ቤት በነበረው በላይኛው በብንያም በር ባለው በመንቈር ውስጥ አሠረው። 3 በነጋውም ጳስኮር ኤርምያስን ከመንቈር ውስጥ ፈታው። ኤርምያስም እንዲህ አለው፦ “ጌታ ስምህን፦ ማጎርሚሳቢብ እንጂ ጳስኮር ብሎ አይጠራህም። 4 ጌታ እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ ለራስህና ለወዳጆችህ ሁሉ ፍርሃት አደርግሃለሁ፤ እነርሱም በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ ዐይኖችህም ያያሉ፤ ይሁዳንም ሁሉ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እርሱም ወደ ባቢሎን ያፈልሳቸዋል በሰይፍም ይገድላቸዋል። 5 የዚህችንም ከተማ ባለጠግነት ሁሉ ጥሪትዋንም ሁሉ ክብርዋንም ሁሉ የይሁዳንም ነገሥታት መዝገብ ሁሉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እነርሱም ይበዘብዙአቸዋል ይዘውም ወደ ባቢሎን ያመጡአቸዋል። 6 አንተም፥ ጳስኮር ሆይ! በቤትህም የሚኖሩት ሁሉ ተማርካችሁ ትሄዳላችሁ፤ አንተም በሐሰት ትንቢት የተናገርህላቸው ወዳጆችህ ሁሉ ወደ ባቢሎን ትገባላችሁ፥ በዚያም ትሞታላችሁ፥ በዚያም ትቀበራላችሁ።” ነቢዩ ኤርምያስ ማጉረምረሙ 7 አቤቱ! አታለልኸኝ እኔም ተታለልሁ፥ ከእኔም በረታህ አሸነፍህም፤ ቀኑን ሁሉ መሳቂያ ሆኛለሁ፥ ሁሉም ያላግጡብኛል። 8 በተናገርሁ ቍጥር እጮኻለሁ፤ “ግፍና ጥፋት” ብዬ እጮኻለሁ፤ የጌታ ቃል ቀኑን ሁሉ ስድብና መዘበቻ ሆኖብኛልና። 9 እኔም፦ “የጌታን ስም አላነሣም፥ ከእንግዲህ ወዲህም በስሙ አልናገርም” ብል፥ በአጥንቶቼ ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት ያለ በልቤ ሆነብኝ፤ ደከምሁ፥ መሸከምም አልቻልሁም። 10 የብዙ ሰዎችን የክፋት ሹክሹክታ ሰምቻለሁ፥ ማስፈራራትም ከብቦኛል። መውደቄን የሚጠብቁ የሰላሜ ሰዎች ሁሉ፦ “ምናልባት ይታለል እንደሆነ፥ እናሸንፈውም እንደሆነ፥ እርሱንም እንበቀል እንደሆነ፥ ክሰሱት እኛም እንከስሰዋለን” ይላሉ። 11 ጌታ ግን እንደ አስፈሪ ተዋጊ ከእኔ ጋር ነው፤ ስለዚህ አሳዳጆቼ ይሰናከላሉ አያሸንፉም፤ አይከናወንላቸውምና በጽኑ እፍረት ያፍራሉ፥ ለዘለዓለምም በማይረሳ ውርደት ይዋረዳሉ። 12 የሠራዊት ጌታ ሆይ! ጻድቅን የምትመረምር ኩላሊትንና ልብን የምትመለከት፥ ሙግቴን ገልጬልሃለሁና በቀልህን በላያቸው ልይ። 13 ለጌታ ዘምሩ ጌታንም አመስግኑ፤ የችግርተኛውን ነፍስ ከክፉ አድራጊዎች እጅ አድኖአልና። 14 የተወለድሁባት ቀን የተረገመች ትሁን! እናቴ እኔን የወለደችባት ቀን የተባረከች አትሁን! 15 “ወንድ ልጅ ተወልዶልሃል” ብሎ ለአባቴ የምሥራች ነግሮ እጅግ ደስ ያሰኘው ሰው የተረገመ ይሁን። 16 ያም ሰው ጌታ ሳይጸጸት እንደ ገለበጣቸው ከተሞች ይሁን፥ በማለዳም ልቅሶን በቀትርም ጩኸትን ይስማ፤ 17 እናቴ መቃብር እንድትሆነኝ ማኅፀንዋም ዘወትር ይዞኝ እንዲቆይ በማኅፀን ውስጥ አልገደለኝምና። 18 ድካምንና ጣርን እንዳይ፥ ዘመኔም በእፍረት እንድታልቅ ለምን ከማኅፀን ወጣሁ? |