ኤርምያስ 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የባእድ አምልኮ በእስራኤል ላይ ጥፋትን ማምጣቱ 1 እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ! ጌታ በእናንተ ላይ የተናገረውን ቃል ስሙ። 2 ጌታ እንዲህ ይላል፦ “የአሕዛብን መንገድ አትማሩ፥ ከሰማይ ምልክቶችም የተነሣ አትፍሩ፤ አሕዛብ ከእነርሱ የተነሣ ይፈራሉና። 3 የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ ዛፍ ከዱር ይቈረጣል፥ በሞያተኛውም እጅ በመጥረቢያ ይሠራል። 4 በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፥ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል። 5 በዱባ እርሻ (የአትክልት ስፍራ) ውስጥ እንዳለ እንደ ወፍ ማስፈራርያ ዓምድ ናቸው፥ እነርሱም አይናገሩም፤ መራመድም ስለማይችሉ ይሸከሙአቸዋል። ክፉ መሥራት አይችሉምና፥ ደግሞም መልካም መሥራት በእነርሱ ውስጥ የለምና አትፍሩአቸው።” 6 ጌታ ሆይ! እንደ አንተ ያለ የለም፤ አንተ ታላቅ ነህ ስምህም በኃይል ታላቅ ነው። 7 የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ! በአሕዛብ ጥበበኞች ሁሉ መካከል በመንግሥታቸውም ሁሉ እንደ አንተ ያለ ስለ ሌለ፥ አንተን መፍራት ይገባልና አንተን የማይፈራ ማን ነው? 8 በአንድ ጊዜ ቂላ ቂሎችና ሞኞች ሆነዋል፤ ጣዖታት የሚያስተምሩት ከግዑዝ እንጨት የማይሻልን ነገር ብቻ ነው። 9 የሞያተኛና የአንጥረኛ እጅ ሥራ የሆነ ከተርሴስ ጥፍጥፍ ብር ከአፌዝም ወርቅ ይመጣል፤ ልብሳቸውም ሰማያዊና ሐምራዊ ነው፥ ሁሉም የብልሃተኞች ሥራ ናቸው። 10 ጌታ ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ ከቁጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ አሕዛብም መዓቱን መቋቋም አይችሉም። 11 እናንተም፦ “ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ እነዚህ አማልክት ከምድር ላይ ከሰማይም በታች ይጠፋሉ” ትሉአቸዋላችሁ። ለጌታ የምስጋና ቃላት 12 ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለምን በጥበቡ የመሠረተ፥ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። 13 ድምፁን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይታወካሉ፥ ከምድርም ዳርቻ ደመናትን ከፍ ያደርጋል፤ ለዝናቡም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል። 14 ሰው ሁሉ ቂላ ቂልና እውቀት የሌለው ሆኖአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና። 15 እነርሱ ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው፤ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ። 16 የያዕቆብ ድርሻ እንደ እነዚህ አይደለም፤ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና፤ ስሙ የሠራዊት ጌታ ነው። ወደ ፊት የኢየሩሳሌም ሕዝብ እንደሚሰደድ 17 በምሽግ ውስጥ የተቀመጥሽ ሆይ! ዕቃሽን ከመሬት ሰብስቢ፤ 18 ጌታ እንዲህ ይላልና፦ “እነሆ፥ በምድሪቱ የሚኖሩትን እስኪሰማቸው ድረስ በዚህ ጊዜ እወነጭፋቸዋለሁ፥ አስጨንቃቸዋለሁም።” 19 ስለ ስብራቴ ወዮልኝ! ቁስሌም የማይሽር ነው፥ እኔ ግን፦ “በእውነት የመከራ ቁስሌ ነው እርሱንም መሸከም ይገባኛል” አልሁ። 20 ድንኳኔ ተበዘበዘ አውታሬም ሁሉ ተቈረጠ፤ ልጆቼም ከእኔ ወጥተው አይገኙም፤ ድንኳኔንም ከእንግዲህ ወዲህ የሚዘረጋ መጋረጃዎችንም የሚያነሣ የለም። 21 እረኞች ቂላ ቂል ሆነዋልና፥ ጌታንም አልጠየቁትምና አልተከናወነላቸውም፥ መንጎቻቸውም ሁሉ ተበትነዋል። 22 የወሬን ድምፅ ስሙ፤ እነሆም፥ የይሁዳን ከተሞች ባድማና የቀበሮ ማደሪያ ሊያደርጋቸው ከሰሜን ምድር ጽኑ ሽብር መጥቷል። ነቢዩ ኤርምያስ ለሕዝብ ያደረገው ጸሎት 23 አቤቱ! የሰው መንገድ ከራሱ እንዳልሆነ አውቃለሁ፥ ሰውም አካሄዱን ለመምራት የሚራመድ አይደለም። 24 አቤቱ! ገሥጸኝ፤ ነገር ግን እንዳታዋርደኝ በመጠን ይሁን እንጂ በቁጣ አይሁን። 25 ያዕቆብን በልተውታልና፥ ውጠውታልምና፥ አጥፍተውታልምና፥ ማደሪያውንም አፍርሰዋልና በማያውቁህ አሕዛብ ስምህንም በማይጠሩ ወገኖች ላይ መዓትህን አውርድ። |