Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ያዕቆብ 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ከዓለም ክፋት መጠንቀቅ

1 በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ ከሚዋጋው ከፍትወት ምኞት አይደለምን?

2 ትመኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙም፤ ስለዚህ ትገድላላችሁ። በብርቱም ትመኛላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም፤ ስለዚህ ትጣላላችሁ፤ ትዋጋላችሁ። ስለማትለምኑ የምትፈልጉትን አታገኙም።

3 የምትለምኑትም ለፍትወታችሁ በማሰብ በክፉ ምኞት ስለሆነ፥ ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም።

4 አመንዝሮች ሆይ! ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላትነት መሆኑን አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።

5 ወይስ “እርሱ በውስጣችን ያሳደረው መንፈስ አብዝቶ ይቀናል” በማለት መጽሐፍ የተናገረው በከንቱ ይመስላችኋልን?

6 ስለዚህ፥ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” እንደሚል፥ የሚሰጠው ጸጋ ግን ከሁሉም ይበልጣል።

7 እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል።

8 ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች! እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ።

9 ተጨነቁ፤ እዘኑ፤ አልቅሱም። ሳቃችሁ ወደ ኀዘን፥ ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ።

10 በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፥ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።


በሰው ላይ መፍረድ እንደማይገባ

11 ወንድሞች ሆይ! እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ፤ ወንድሙን የሚወነጅልና በወንድሙም ላይ የሚፈርድ በሕግ ላይ ክፉ ይናገራል፤ በሕግም ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ ብትፈርድ ፈራጅ እንጂ ሕግን ፈጻሚ አይደለህም።

12 ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ሊያድንና ሊያጠፋ የሚችል ነው፤ ነገር ግን በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?


ስለ ትምክሕት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

13 እናንተ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ወይም ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በእርሷም አንድ ዓመት እንቈያለን፤ እንነግዳለን፤ እናተርፋለንም” የምትሉ ተመልከቱ፤

14 ነገ የሚሆነውን አታውቁም። ሕይወታችሁ ምንድነው? ለጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት አይደላችሁምን?

15 ይልቁንም፥ “የጌታ ፈቃድ ቢሆን እንኖራለን፤ ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን” ማለት ይገባችኋል።

16 እናንተ ግን በእብሪታችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲህ ያለው ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው።

17 እንግዲህ መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ እንዳለበት እያወቀ የማያደርግ ሰው ኃጢአት ያደርጋል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች