Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ያዕቆብ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


አንደበትን ስለ መቈጣጠር

1 ወንድሞቼ ሆይ! ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፤ ምክንያቱም አስተማሪዎች የሆንን የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል ታውቃላችሁ።

2 ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር እርሱ ሰውነቱን ሁሉ መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው።

3 ፈረሶች እንዲታዘዙልን ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናስገባለን፤ መላ ሰውነታቸውንም መምራት እንችላለን።

4 መርከቦችንም ተመልከቱ፤ ምንም እንኳ እጅግ ትልቅና በኀይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይመራቸዋል።

5 እንዲሁም ምላስ ትንሽ የሰውነት ክፍል ሆና ሳለች በታላላቅ ነገሮች ትኩራራለች፤ ትልቅ ጫካ በትንሽ እሳት እንዴት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ አስተውሉ፤

6 ምላስም እንደ እሳት ናት፤ በሰውነት ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ የክፋት ዓለም ናት፤ ሰውነትን ሁሉ ታረክሳለች፤ ደግሞም የፍጥረትን ሩጫ ታቃጥላለች፤ ራሷም በገሃነም ትቃጠላለች።

7 ማናቸውም ዓይነት አውሬ፥ አዕዋፍ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡና በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ መገራት ችለዋል፤ በሰውም ተገርተዋል።

8 ነገር ግን ምላስን መግራት የሚችል ማንም ሰው የለም፤ የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት።

9 በምላሳችን ጌታንና አብን እንባርካለን፥ በእርሷም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን።

10 ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ፤ ወንድሞቼ ሆይ! ይህ ሊሆን አይገባም።

11 ከአንድ ምንጭ ጣፋጭ ውሃና መራራ ውሃ ይመነጫልን?

12 ወንድሞቼ ሆይ! የበለስ ዛፍ የወይራን ፍሬ ሊያፈራ ይችላልን? ወይስ የወይን ተክል የበለስ ፍሬ ሊያፈራ ይችላልን? እንዲሁም ከጨው ውሃ ጣፋጭ ውሃ ሊገኝ አይችልም።


ሰማያዊ ጥበብ

13 ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ የሆነ ማን ነው? በመልካም አኗኗር ሥራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ።

14 ነገር ግን መራራ ቅናትና ራስ ወዳድነት በልባችሁ ቢኖር ኩራት አይሰማችሁ፤ በእውነትም ላይ አትዋሹ።

15 እንዲህ ያለችዋ ጥበብ ከላይ አይደለችም፤ ነገር ግን ምድራዊ፥ ሥጋዊና አጋንንታዊ ናት።

16 ቅናትና ራስ ወዳድነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ ይኖራሉ።

17 ከላይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ ቀጥሎም ሰላም ወዳድ፥ ደግ፥ እሺ ባይ፥ ምሕረትና መልካም ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።

18 የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉ በሰላም ይዘራል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች