ኢሳይያስ 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ለንጉሥ አካዝ የመጣለት መልእክት 1 የዖዝያን የልጅ ልጅ፤ የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን፤ የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ ነገር ግን ድል ሊያደርጓት አልቻሉም። 2 ለዳዊት ቤት፤ “ሶርያና ኤፍሬም ተባብረዋል” የሚል ወሬ በደረሰ ጊዜ፤ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ የአካዝና የሕዝቡ ልብ እንዲሁ ተናወጠ። 3 ጌታም ኢሳይያስን እንዲህ አለው፤ “‘አንተና ልጅህ ሸአር-ያሹብ አካዝን ለመገናኘት ወደ ልብስ አጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኩሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤’” 4 እንዲህም በለው፤ “‘ተጠንቀቅ፤ ተረጋጋ፤ አትፍራ በእነዚህ ከእሳት ተርፈው በሚጤሱት በሁለቱ የዕንጨት ጉማጆች፤ በሶርያና በንጉሷ በረአሶን እንዲሁም በሮሜልዩ ልጅ ቁጣ አትሸበር።’ 5 ሶርያ ኤፍሬምና፤ የሮሜልዩ ልጅ ሊያጠፉህ እንዲህ ብለው ተማከሩ፤ 6 ‘ይሁዳን እንውረር፤ እንበታትነው ተከፋፍለንም እንግዛው፤ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥበት።’ 7 ልዑል እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፦ ‘ይህ ምክራቸው አይፈጸምም፤ ከቶም አይደረግም፤ 8 የሶርያ ራስ ደማስቆ፤ የደማስቆ ራስ ረአሶን ነውና፤ በሥልሳ አምስት ዓመት ውስጥ፤ የኤፍሬም ሕዝብ ይበታተናል፤ ሕዝብ መሆኑም ይቀራል። 9 የኤፍሬም ራስ ሰማርያ፤ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። እንግዲህ በእምነታችሁ ካልጸናችሁ፤ ፈጽሞ መቆም አትችሉም።’ 10 እንደገናም ጌታ አካዝን እንዲህ አለው፤ 11 ‘ከጥልቁ ጥልቅ ወይም ከከፍታው ከፍታ ምልክት እንዲሰጥህ ከጌታ ከአምላክህ ለምን።’ 12 አካዝ ግን፤ አልለምንም፤ ጌታንም አልፈታተንም” አለ። 13 ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፤ ስሙ፤ የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላኬን ትዕግሥት ትፈታተናላችሁን? 14 ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። 15 ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ሲችል ቅቤና ማር ይበላል። 16 ነገር ግን ሕፃኑ ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ባድማ ይሆናል። 17 ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፤ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የሚያመጣውም የአሦርን ንጉሥ ነው። 18 በዚያን ቀን ጌታ ራቅ ካሉት ከግብጽ ወንዞች ዝንቦችን፤ ከአሦርም ምድር ንቦችን በፉጨት ይጠራል። 19 እነርሱም በሙሉ መጥተው፤ በየበረሓው ሸለቆ፤ በየዐለቱ ንቃቃት፤ በየእሾኩ ቁጥቋጦና በየውሃው ጉድጓድ ሁሉ ይሰፍራሉ። 20 በዚያን ቀን፤ እግዚአብሔር ከወንዝ ማዶ በተከራየው ምላጭ፤ ማለትም በአሦር ንጉሥ፤ የራስና የእግር ጠጉራችሁን እንዲሁም ጢማችሁን ይላጫል። 21 በዚያን ቀን፤ አንድ ሰው አንዲት ጊደርና ሁለት በግ ብቻ ይተርፈዋል። 22 ከሚሰጡትም የተትረፈረፈ ወተት ቅቤ ይበላል፤ በምድሪቱም የቀሩ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላሉ። 23 በዚያን ቀን ሺህ ሰቅል ብር የሚያወጣ አንድ ሺህ የወይን ተክል የነበረበት ቦታ ሁሉ፤ ኩርንችትና እሾኽ ብቻ ይሆናል። 24 ምድሪቱ በኩርንችትና በእሾኽ ስለምትሸፈን፤ ሰዎች ወደዚያ የሚገቡት ቀስትና ፍላጻ ይዘው ነው፤ 25 ኩርርንችትና እሾኹን በመፍራት ከዚህ በፊት በመቈፈሪያ ተቈፍረው ወደነበሩት ወደ እነዚያ ኰረብታዎች ሁሉ ከእንግዲህ አትሄድም፤ ነገር ግን የከብቶች መሰማሪያና የበጎች መፈንጫ ቦታ ይሆናሉ።” |