Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ኢሳይያስ 44 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 አሁንም አገልጋዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማ።

2 የፈጠረህ ከማኅፀንም የሠራህ የሚረዳህም ጌታ እንዲህ ያልል፦ አገልጋዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም ይሹሩን ሆይ፥ አትፍራ።

3 በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈሳለሁ፥

4 በፈሳሾችም አጠገብ እንደሚበቅሉ እንደ አኻያ ዛፎች በሣር መካከል ይበቅላሉ።

5 ይህ፦ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ይላል፥ ያም በያዕቆብ ስም ይጠራል፤ ይህም፦ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእጁ ይጽፋል፤ በእስራኤልም የቁልምጫ ስም ይጠራል።

6 የእስራኤል ንጉሥ ጌታ፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ ፊተኛ ነኝ፥ እኔ ፍጻሜም ነኝ፤ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም።

7 እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ ይናገርም፤ ከጥንት የፈጠርሁትን ሕዝብ ያዘጋጅልኝ፥ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይንገረኝ።

8 አትፍሩ አትደንግጡም፤ ከጥንቱም ጀምሬ አልነገርኋችሁም? ወይስ አላሳየኋችሁም? እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ ሌላ አምላክ አለን? ሌላ ዐለት የለም፤ አንድም አላውቅም።


የጣዖት አምላኪዎች ከንቱነት

9 የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ከንቱዎች ናቸው፤ የወደዱትም ነገር አይጠቅማቸውም፤ ምስክሮቻቸውም አያስተውሉም ደግሞ አያውቁም፥ ስለዚህ ያፍራሉ።

10 ጣዖትን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባን ምስልን የቀረጸ ማን ነው?

11 እነሆ፥ ባልንጀሮቹ ሁሉ ያፍራሉ፥ ባለሙያዎቹም ከሰው ወገን ናቸው፤ ሁሉም ተሰብስበው ይቁሙ፤ ይፈራሉ በአንድነትም ያፍራሉ።

12 ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይሠራል፥ በፍምም ውስጥ ያደርገዋል፥ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሠጠዋል፤ በክንዱም ኃይል ይሠራዋል፥ እርሱም ይርበዋል ይደክማልም፤ ውኃም ለመጠጣት ይታክታል።

13 ጠራቢው ገመድ ይዘረጋል፥ በጠመኔም ምልክት ያኖራል፥ በመሮም ይቀርጸዋል፥ በመለኪያም ይለከዋል፤ በቤትም ውስጥ እንዲቀመጥ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ይቀርጸዋል።

14 የዝግባን ዛፎች ይቈርጣል፤ የዞጲንና የኮምቦልን ዛፍ ይመርጣል፥ ከዱር ዛፎችም መካከል እንዲጠነክር ይተወዋል፤ የጥድንም ዛፍ ይተክላል፥ ዝናብም ያበቅለዋል።

15 ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፥ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፤ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል።

16 ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፥ በዚያ በግማሹ ሥጋ ይበላል፤ ሥጋም ይጠብስበትና ይጠግባል፤ ይሞቃልና፦ “እሰይ ሞቅሁ፥ ሙቀት ተሰማኝ” ይላል።

17 የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግድበታል፤ ወደ እርሱም እየጸለየ፦ አምላኬ ነህና አድነኝ ይላል።

18 አያውቁም፥ አያስቡም፤ እንዳያዩ ዐይኖቻቸውን፥ እንዳያስተውሉም ልቦቻቸውን ጨፍነዋል።

19 በልቡም ማንም አያስብም፦ “ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፥ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፥ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፤ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን?” ለማለት እንኳን እውቀትና ማስተዋል የለውም።

20 አመድ ይበላል፥ የተታለለ ልብ አስቶታል፥ ነፍሱን ለማዳን አይችልም፥ ወይም፦ “በቀኝ እጄ ሐሰት አለ?” ብሎም አይጠይቅም።

21 ያዕቆብ ሆይ፥ አንተም እስራኤል፥ አገልጋዬ ነህና ይህን አስብ፤ እኔ ሠርቼሃለሁ አንተም አገልጋዬ ነህ፤ እስራኤል ሆይ፥ በእኔ ዘንድ ያልተረሳህ ትሆናለህ።

22 መተላለፍህን እንደ ደመና፥ ኃጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፤ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ።

23 ሰማያት ሆይ፥ ጌታ አድርጎታልና ዘምሩ፤ ጌታ ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና አንተ የምድር ጥልቅ ሆይ፥ ጩኽ፤ እናንተም ተራሮች አንተም ዱር በአንተም ያለ ዛፍ ሁሉ፥ እልል በሉ።

24 ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ ጌታ እኔ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?

25 የሐሰተኞችን ምልክት ከንቱ አደርጋለሁ፥ ምዋርተኞችንም አሳብዳለሁ፥ ጥበበኞቹንም ወደ ኋላ እመልሳለሁ፥ እውቀታቸውንም ስንፍና አደርጋለሁ፤

26 የባርያዬን ቃል አጸናለሁ፤ የመልእክተኞቼንም ምክር እፈጽማለሁ፤ ኢየሩሳሌምን፦ የሰው መኖሪያ ትሆኛለሽ፥ የይሁዳንም ከተሞች፦ ትታነጻላችሁ ፍራሾቻችሁንም አቆማለሁ እላለሁ።

27 ቀላዩም፦ “ደረቅ ሁን፥ ፈሳሾችህንም አደርቃለሁ” እላለሁ፤

28 ቂሮስንም፦ “እርሱ እረኛዬ ነው”፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን፦ “ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል” ይላል፤ እኔም “ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል” እላለሁ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች