ኢሳይያስ 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 በዚያን ቀን ሰባት ሴቶች አንዱን ወንድ ይዘው፤ “የራሳችንን ምግብ እንበላለን፤ የራሳችንንም ልብስ እንለብሳለን፤ በአንተ ስም ብቻ እንጠራና፤ ውርደታችንን አስቀርልን” ይሉታል። የጌታ ዛፍ ቅርንጫፍ 2 በዚያን ቀን የጌታ ዛፍ ቅርንጫፍ ውብና የከበረ ይሆናል፤ የምድሪቱም ፍሬ ከጥፋት ለተረፈው የእስራኤል ወገን 3 በጽዮን የቀሩት፤ በኢየሩሳሌምም የተረፉት፤ በኢየሩሳሌም በሕይወት ከተመዘገቡት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ተብለው ይጠራሉ፤ ኩራትና ክብርም ይሆናል። 4 ጌታ የጽዮንን ሴቶች እድፍ ያጥባል፤ ኢየሩሳሌምንም ከተነከረችበት ደም በፍርድና በሚያቃጥል መንፈስ ያነጻታል። 5 ከዚያም ጌታ በጽዮን ተራራ ላይና በዚያ በሚሰበሰቡትም ሁሉ ላይ በቀን ደመናንና ጢስን፤ በሌሊትም የሚንበለበለውን የእሳት ብርሃን ይፈጥራል፤ በክብሩ ሁሉ ላይ መጋረጃ ይሆናል፤ 6 ከቀኑ ሙቀት ጥላና መከለያ፤ ከውሽንፍርና ከዝናብም መጠጊያና መሸሸጊያ ስፍራ ይሆናል። |