Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ኢሳይያስ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የሚመጣ ፍርድ

1 እነሆ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ድጋፉንና ርዳታውን፤ የምግብና የውሃ ርዳታውን ሁሉ ይነሣል፤

2 ጀግናውንና ተዋጊውን፤ ፈራጁንና ነቢዩን፤ አስማተኛውንና ሽማግሌውን፤

3 የአምሳ አለቃውንና ባለ ማዕረጉን፤ አማካሪውንና ጠቢቡን የእጅ ባለሙያ፤ ብልኁንም ምትሀተኛ ይነሣል።

4 ልጆችን መሪዎቻቸው አደርጋለሁ፤ ያልበሰሉ ሕፃናትም ይገዟቸዋል።

5 ሕዝብ እርስ በርሱ ይጨቋቈናል፤ ሰው በሰው ላይ፤ ባልንጀራ በባልንጀራው ላይ፤ ወጣቱ በሽማግሌው ላይ፤ ተራው ሰው በተከበረው ላይ ይነሣል።

6 ሰውም በአባቱ ቤት ከወንድሞቹ አንዱን ይዞ፤ “አንተ ልብስ ስላለህ መሪ ሁነን፤ ይህንንም የፍርስራሽ ክምር ግዛ” ይለዋል።

7 እርሱ ግን በዚያ ቀን ድምጽን ከፍ አድርጎ፤ “እኔ መፍትሔ አልሆንም፤ በቤቴም ልብስና ምግብ የለኝም፤ የሕዝብ መሪ አታድርጉኝ” ይላል።

8 ኢየሩሳሌም ተንገዳገዳለች፤ ይሁዳም ለመውደቅ ተቃርባለች፤ ንግግራቸውም ሆነ ድርጊታቸው ጌታን የሚቃወም፤ የክብሩንም መገኘት የሚያቃልል ነውና።

9 የፊታቸው ገጽታ ይመሰክርባቸዋል፤ ኀጢአታቸውን እንደ ሰዶም በይፋ ይናገራሉ፤ አይደብቁትምም፤ ጥፋትን በራሳቸው ላይ ስላመጡ ወዮላቸው!

10 ጻድቃን መልካም ነገር እንደሚያገኙ ንገሯቸው፤ የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና። የእጃቸውን ያገኛሉና።

11 በደለኞች ወዮላቸው፤ ጥፋት ይመጣባቸዋል፤

12 ወጣቶች ሕዝቤን ያስጨንቃሉ፤ ሴቶችም ይገዟቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፤ መሪዎችህ አሳስተውሃል፤ ከመንገድህም መልሰውሃል።

13 ጌታ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦአል፤ በሕዝቡም ላይ ለመፍረድ ተነሥቶአል።

14 ጌታ ከአለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ጋር እንዲህ ሲል ይፋረዳል፤ “የወይኔን ቦታ ያጠፋችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድኾች የዘረፋችሁትም በቤታችሁ ይገኛል፤

15 ሕዝቤን በችግር ስታደቁት፤ የድኾችንም ፊት በኀዘን ስታገረጡት ምን ማለታችሁ ነው?” ይላል ጌታ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

16 ጌታ እንዲህ ይላል፤ የጽዮን ሴቶች ኰርተዋል፤ ዐንገታቸውን እያሰገጉ፤ በዐይናቸውም እየጠቀሱ ይሄዳሉ፤ እየተቈነኑ በመራመድ፤ የእግራቸውን ዐልቦ ያቃጭላሉ።

17 ስለዚህ፤ ጌታ በጽዮን ሴቶች ዐናት ላይ ቆረቆር ያመጣል፤ ጌታም ራሳቸውን ቡሀ ያደርጋል።

18 በዚያም ቀን ጌታ የክብር ጌጣቸውን ይነጥቃቸዋል፤ የእግር አንባሩን፤ የጠጉር ጌጡን፤ የጨረቃ ቅርጽ ያለውን የዐንገት ጌጥ፤

19 የጆሮ ጉትቻውን፤ የእጅ አንባሩን፤ የፊት መሸፈኛውን፤

20 የራስ መሸፈኛውን፤ ዐልቦውን፤ ሻሹን፤ የሽቶ ብልቃጡን፤ አሸን ክታቡን፤

21 የጣት ቀለበቶችንና የአፍንጫ ቀለበቶችን፤

22 ያማረውን ቀሚስ፤ የውስጥ ልብሱን፤ ካባውን፤ የእጅ ቦርሳውን፤

23 መስታወቱን፤ ከጥሩ በፍታ የተሠራውን ልብስ፤ የራስ ጌጡን፤ ዐይነ ርግቡን ሁሉ ይነጥቃቸዋል።

24 በሽቶ ፈንታ ግማት፤ በሻሽ ፈንታ ገመድ፤ አምሮ በተሠራ ጠጉር ፈንታ ቡሀነት፤ ባማረ ልብስ ፈንታ ማቅ፤ በውበትም ፈንታ ጠባሳ ይሆናል።

25 ወንዶቻችሁ በሰይፍ ስለት፤ ተዋጊዎቻችሁ በጦርነት ይወድቃሉ።

26 የጽዮን ደጆች ያዝናሉ፤ ያለቅሳሉም፤ እርሷም ተረስታ በመሬት ላይ ትቀመጣለች።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች