Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ኢሳይያስ 29 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ዳዊት የሰፈረብሽ ከተማ አርኤል፥ አንቺ አርኤል ወዮልሽ! ዓመት በዓመት ላይ ጨምሩ፥ በዓላትም ይመላለሱ።

2 ግን አርኤልንም አስጨንቃለሁ፥ ልቅሶና ዋይታም ይሆንባታል፤ እሷም እንደ አርኤል ትሆንልኛለች።

3 በዙሪያሽም እሰፍራለሁ፥ በቅጥርም ከብቤ አስጨንቅሻለሁ፥ የጥበቃ አምባም በላይሽ አቆማለሁ።

4 ትዋረጃለሽ፥ መሬት ላይ ተደፍተሽ ትናገሪያለሽ፥ ቃልሽም በዝግታ ከአፈር ይወጣል፤ ድምጽሽም ከመሬት እንደሚወጣ እንደ መናፍስት ድምፅ ይሆናል፥ ንግግርሽም ከአፈር በሹክሹክታ ይወጣል።

5 ነገር ግን የጠላቶችሽ ብዛት እንደ ደቀቀ ትቢያ፥ የጨካኞችም ብዛት እንደሚያልፍ ገለባ ይሆናል።

6 ድንገትም ፈጥኖ የሠራዊት ጌታ በነጐድጓድ፥ በምድርም መናወጥ፥ በታላቅም ድምፅ፥ በዐውሎ ነፋስም፥ በወጨፎም፥ በምትበላም በእሳት ነበልባል ይጐበኛታል።

7 በአርኤልም ላይ የሚዋጉ፥ እርሷንና ምሽግዋንም የሚወጉ የሚያስጨንቋትም፥ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት እንደ ሕልምና፥ እንደ ሌሊት ራእይ ይሆናል።

8 ተርቦም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፤ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይበላል፥ ነገር ግን ይነቃል ሰውነቱም ባዶ ነው፤ ተጠምቶም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፤ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይጠጣል፥ ነገር ግን ይነቃል፥ እነሆም፥ ይዝላል ሰውነቱም እንደተጠማ አለ፤ የጽዮንን ተራራም የሚወጉ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት እንደዚሁ ይሆናል።

9 ተደነቁ ደንግጡም፤ ጨፍኑ ታወሩም! ስክሩም፥ በወይን ጠጅ አይደለም፤ ተንገዳገዱ፥ በመጠጥ አይደለም።

10 ጌታ የሚደብት የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋል፤ ዐይኖቻችሁን፥ ነቢያትንም ጨፍኖባችኋል፤ ራሶቻችሁን ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል።

11 ይህ ሁሉ ራእይ እንደ ታተመ የመጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ፦ “ይህን አንብብ” ብለው ባዘዙት ጊዜ እርሱ፦ “ታሽጓልና አልችልም” ይላቸዋል፤

12 ደግሞም መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ፦ “ይህን አንብብ” ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፦ “ማንበብ አላውቅም” ይላቸዋል።

13 ጌታም፦ ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፥ በከንፈሮቹም ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛል።

14 ስለዚህ፥ እነሆ፥ ድንቅ ነገርን በዚህ ሕዝብ መካከል፥ አስደማሚ ነገርን ተአምራትንም እንደገና አደርጋለሁ፤ የጥበበኞችም ጥበብ ትጠፋለች፥ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትሰወራለች።

15 ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከጌታ ለሚሰውሩ፥ ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው፦ “ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀናል?” ለሚሉ ወዮላቸው!

16 ይህ የእናንተ ጠማምነት ነው፤ እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቈጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን፦ “አልሠራኸኝም” ይለዋልን? ወይስ የተደረገው አድራጊውን፦ “አታስተውልም” ይለዋልን?

17 ሊባኖስ እንደ ፍሬያማ እርሻ ሊለወጥ ፍሬያማውም እርሻ እንደ ዱር ሊቆጠር ጥቂት ዘመን ቀርቶት የለምን?

18 በዚያም ቀን ደንቆሮዎች የመጽሐፍን ቃል ይሰማሉ፥ የዕውሮችም ዐይኖች ጭጋግና ጨለማው ተገፎላቸው ያያሉ።

19 የዋሃን ደስታቸውን በጌታ ያበዛሉ፥ በሰዎች መካከል ያሉ ችግረኞችም ሐሤትን በእስራኤል ቅዱስ ያደርጋሉ።

20 ጨካኙ ሰው አልቆአልና፥ ፌዘኛውም ጠፍቷልና፥ ለኃጢአትም ያደፈጡ ሁሉ ይቈረጣሉ፤

21 እነርሱም ሰውን በነገር በደለኛ የሚያደርጉ፥ በበርም ለሚገሥጸው አሽክላ የሚያኖሩ፥ ጻድቁንም በከንቱ ነገር የሚያስቱ ናቸው።

22 ስለዚህ አብርሃምን የተቤዠ ጌታ ስለ ያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፦ ያዕቆብ አሁን አያፍርም፥ ፊቱም አሁን አይለወጥም።

23 ነገር ግን የእጄን ሥራ ልጆቹን በመካከሉ ባያቸው ጊዜ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የያዕቆብንም ቅዱስ ይቀድሳሉ፥ የእስራኤልንም አምላክ ይፈራሉ።

24 በመንፈስም የሳቱ ወደ ማስተዋል ይደርሳሉ፤ የሚያጉረመርሙም ምክርን ይቀበላሉ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች