Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ኢሳይያስ 18 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


በኢትዮጵያ ላይ የተነገረ ትንቢት

1 በኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ ላለች፥ ክንፍ ያላቸው መርከቦች ላሉባት፥

2 መልእክተኞችን በባሕር ላይ፥ የደንገል መርከቦችንም በውኃ ላይ ለምትልክ ምድር ወዮላት! እናንተ ፈጣን መልእክተኞች ሆይ፥ ወደ ረጅምና ወደ ለስላሳ ሕዝብ፥ ከቅርብም ከሩቅም አስፈሪ ወደ ሆነ ሕዝብ፥ ኀያል ወደሆነና ወደሚገዛ፥ ወንዞችም ምድራቸውን ወደሚከፍሉት ሕዝብ ሂዱ።

3 እናንት በዓለም ውስጥ ያላችሁና በምድር የምትኖሩ ሕዝቦች ሆይ፥ ምልክት በተራሮች ላይ በሚወጣ ጊዜ ተመልከቱ! መለከትም በተነፋ ጊዜ ስሙ!

4 ጌታ፥ “በፀሐይ ጮራ እንደ ደረቅ ትኩሳት፥ በአጨዳም ወራት እንደ ጠል ደመና ሆኜ በማደሪያዬ በጸጥታ ተቀምጬ እመለከታለሁ” ብሎኛል።

5 እርሱ ከመከር በፊት አበባ በረገፈ ጊዜ፥ አበባው ያበበ የወይንም ፍሬ ሲይዝ፥ የወይኑን ዘንግ በመግረዣ ይገርዘዋል፤ ጫፎቹንም መልምሎ ያስወግዳል።

6 በተራራ ላይ ላሉ ነጣቂ ወፎች፥ ለምድርም አውሬዎች ይተዋሉ። ነጣቂ ወፎችም በጋውን ሁሉ ይበጁባቸዋል፤ የምድርም አውሬዎች ክረምቱን ሁሉ ሲበሉት ይከርማሉ።

7 በዚያን ጊዜ ለሠራዊት ጌታ፥ ከረጅምና ከለስላሳ ሕዝብ፥ ከቅርብም ከሩቅም አስፈሪ ከሆነ ሕዝብ፥ ኀያል ከሆነና ከሚገዛ፥ ወንዞችም ምድራቸውን ከሚከፍሉት ሕዝብ ዘንድ ስጦታ ይመጣለታል፤ ስጦታውም የሠራዊት ጌታ ስም ወደሚገኝበት ወደ ጽዮን ተራራ ይቀርባል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች