ኢሳይያስ 14 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ጌታ ግን ያዕቆብን ይምረዋል፥ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፥ በአገራቸውም ያኖራቸዋል፤ መጻተኛም ከእርሱ ጋር ይተባበራል፥ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይተሳሰራል። 2 አሕዛብም ይዘው ወደ ስፍራቸው ያመጡአቸዋል፥ የእስራኤልም ቤት በእግዚአብሔር ምድር እንደ ሎሌዎችና እንደ ገረዶች አድርገው ይገዙአቸዋል፤ የማረኩአቸውን ይማርካሉ፥ አስጨናቂዎችንም ይገዛሉ። የባቢሎን ንጉሥ ውድቀት 3 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ጌታ ከኀዘንህና ከመከራህ ከተገዛህለትም ከጽኑ ባርነት ያሳርፍሃል። 4 ይህንም ምሳሌ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ታነሣለህ እንዲህም ትላለህ፦ አስጨናቂ እንዴት አበቃለት! አስገባሪነቱስ እንዴት አከተመ! 5 ጌታ የክፉዎችን ዘንግ፥ የገዢዎችንም በትረ መንግሥት ሰብሯል። 6 ሕዝቦችንም በማያቋርጥ ቁጣ የመታውን፥ ያለ ርኅራኄ ያለማቋረጥ ቀጥቅጦ አሕዛብን በማይበርድ ቁጣው የገዛውን ሰብሮአል። 7 ምድርም ሁሉ አርፋ በጸጥታ ተቀምጣለች እልልም ብላለች። 8 ጥድና የሊባኖስ ዝግባ፦ አንተ ከተዋረድህ ጀምሮ ማንም ይቈርጠን ዘንድ አልወጣብንም ብለው በአንተ ደስ አላቸው። 9 ሲኦል በመምጣትህ ልትገናኝህ በታች ታወከች፤ የሞቱትንም፥ የምድርንም ታላላቆች ሁሉ፥ ለአንተ አንቀሳቀሰች፥ የአሕዛብንም ነገሥታት ሁሉ ከዙፋኖቻቸው አስነሣች። 10 እነዚህ ሁሉ፦ አንተ ደግሞ እንደ እኛ ደክመሃልን? እኛንስ መስለሃልን? 11 ጌጥህና የበገናህ ድምፅ ወደ ሲኦል ወረደ፤ በበታችህም ብል ተነጥፎአል፥ ትልም መደረቢያህ ሆኖአል ብለው ይመልሱልሃል። 12 አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴትስ ወደ ምድር ተጣልክ! 13 አንተም በልብህ፦ ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤ 14 ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ። 15 ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጉድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ። 16 የሚያዩህ ይመለከቱሃልና፦ በውኑ ምድርን ያንቀጠቀጠ፥ መንግሥታትንም ያናወጠ፥ 17 ዓለሙን ባድማ ያደረገ፥ ከተሞችንም ያፈረሰ፥ ምርኮኞቹንም ወደ ቤታቸው ያልላከ ሰው ይህ ነውን? ብለው ያስተውሉሃል። 18 የአሕዛብ ነገሥታት ሁሉ በየቤታቸው በክብር አንቀላፍተዋል። 19 አንተ ግን እንደ ተጠላ ቅርንጫፍ ከመቃብርህ ተጥለሃል፤ በሰይፍም የተወጉት፥ ተገድለውም ወደ ጉድጓዱ ድንጋዮች የወረዱ ከድነውሃል፤ እንደተረገጠም ሬሳ ሆነሃል። 20 ምድርህን አጥፍተሃልና፥ ሕዝብህንም ገድለሃልና ከእነርሱ ጋር በመቃብር በአንድነት አትሆንም፤ የክፉዎች ዘር ለዘለዓለም የተጠራ አይሆንም። 21 እንዳይነሱም፥ ምድርንም እንዳይወርሱ፥ የዓለሙንም ፊት በከተሞች እንዳይሞሉ ስለ አባቶቻቸው በደል ለልጆቹ ሞትን አዘጋጁላቸው። 22 በእነርሱ ላይ እነሣለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ከባቢሎን ስምንና ቅሬታን፥ ዘርንና ትውልድንም እቈርጣለሁ ይላል ጌታ። 23 የጃርት መኖርያ የውሃም መቋሚያ አደርጋታለሁ፤ በጥፋትም መጥረጊያ እጠርጋታለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 24 የሠራዊት ጌታ እንዲህ ብሎ ምሏል፦ “እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፥ እንዳሰብሁም እንዲሁ ይቆማል። 25 አሦርን በምድሬ ላይ እሰብራለሁ፥ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፤ ቀንበሩም ከእነርሱ ላይ ይነሳል፥ ሸክሙም ከጫንቃቸው ላይ ይወገዳል። 26 በምድር ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያሰበው አሳብ ይህ ነው፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋች እጅ ይህች ናት።” በፍልስጤማዊያን ላይ የተነገረ ትንቢት 27 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን አስቦአል፤ የሚያስጥለውስ ማን ነው? እጁም ተዘርግታለች፤ የሚመልሳትስ ማን ነው? 28 ንጉሡ አካዝ በሞተበት ዘመን ይህ ሸክም ሆነ። 29 ፍልስጥኤም ሆይ፥ ከእባቡ ሥር እፉኝት ይወጣልና፥ ፍሬውም የሚበርርና እሳት የሚመስል እባብ ይሆናልና የመታሽ በትር ስለ ተሰበረ ሁላችሁም ደስ አይበላችሁ። 30 የድሆችም የበኩር ልጆች ይሰማራሉ፥ ችግረኞችም ተዘልለው ይተኛሉ፤ ሥርህንም በራብ እገድላለሁ፥ ቅሬታህም ይገደላል። 31 አንተ በር ሆይ፥ ወዮ በል፥ አንቺም ከተማ ሆይ፥ ጩኺ፤ ፍልስጥኤም ሆይ፥ ሁላችሁም ቀልጣችኋል፤ ጢስ ከሰሜን ይመጣል ከጭፍራውም ተለይቶ የሚቀር የለም። 32 ለሕዝቡም መልእክተኞች ምን ብሎ መልስ ይሰጣል? “ጌታ ጽዮንን መሥርቷል፥ ከሕዝቡም ችግረኞች በእርሷ ውስጥ መጠጊያን ያገኛሉ።” |