ሆሴዕ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የእስራኤል መታደስ 1 የእስራኤልም ልጆች ቍጥር እንደማይሰፈርና እንዳማይቆጠር እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፤ እንዲሁም እነርሱ፦ “ሕዝቤ አይደላችሁም” በተባሉበት በዚያ ስፍራ፦ “የሕያው አምላክ ልጆች” ይባላሉ። 2 የይሁዳ ልጆችና የእስራኤል ልጆች በአንድነት ይሰበሰባሉ፥ እነርሱም አንድ አለቃ በራሳቸው ላይ ይሾማሉ፤ የኢይዝራኤልም ቀን ታላቅ ይሆናልና ከምድሪቱ ይወጣሉ። 3 ወንድሞቻችሁን፦ “ዓሚ”፥ እኅቶቻችሁንም፦ “ሩሃማ” በሉአቸው። የእስራኤል አለመታመን፥ መቀጣትና መዳን 4 እናታችሁ ሚስቴ አይደለችምና፥ እኔም ባሏ አይደለሁምና ተምዋገቱ፤ ከእናታችሁ ጋር ተምዋገቱ። ምንዝርናዋን ከፊትዋ፥ ዝሙትዋንም ከጡቶችዋ መካከል ታስወግድ፤ 5 አለበለዚያ ዕራቁትዋን እንድትሆን እገፍፋታለሁ፥ እንደ ተወለደችበትም ቀን አደርጋታለሁ፥ እንደ ምድረ በዳና እንደ ደረቅ ምድር አደርጋታለሁ፥ በጥምም እገድላታለሁ። 6 እንዲሁም የአመንዝራ ልጆች ናቸውና ለልጆችዋ አልራራም። 7 እናታቸው አመንዝራለች፤ የፀነሰቻቸውም እርሷ አሳፋሪ ነገር አድርጋለች፤ ምክንያቱም፦ እንጀራዬንና ውኃዬን፥ ጥጤንና የተልባ እግሬን፥ ዘይቴንና መጠጤን ከሚሰጡኝ ከውሽሞቼ በኋላ እሄዳለሁ፥ ብላለችና። 8 ስለዚህ፥ እነሆ፥ መንገድሽን በእሾህ እዘጋለሁ፤ መንገድዋንም እንዳታገኝ ቅጥርን እቀጥርባታለሁ። 9 ውሽሞችዋንም ትከተላለች፥ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸዋለችም፥ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ እርሷም፦ ከዛሬ ይልቅ የዚያን ጊዜ ይሻለኝ ነበርና፥ ተመልሼ ወደ ቀደመው ባሌ እሄዳለሁ፥ ትላለች። 10 እርሷም እህልንና ወይን ጠጅን ዘይትንም የሰጠኋት፥ ለበኣልም ያደረጉትን ብርና ወርቅ ያበዛሁላት እኔ እንደሆንኩ አላወቀችም። 11 ስለዚህ እህሌን በጊዜው፥ ወይን ጠጄንም በወቅቱ ፈጽሞ እወስዳለሁ፥ ዕራቁትነትዋንም መሸፈኛ የነበረውን ጥጤንና የተልባ እግሬን እገፍፋታለሁ። 12 እንዲሁም አሁን ውሽሞችዋ እያዩ ነውርዋን እገልጣለሁ፤ ከእጄም ማንም አያድናትም። 13 ደስታዋንም ሁሉ፥ በዓላቶችዋንም፥ መባቻዎችዋንም፥ ሰንበቶችዋንም፥ የተቀደሱትንም ጉባኤዎችዋን ሁሉ አስቀራለሁ። 14 እርሷም፦ “ውሽሞቼ ለእኔ የሰጡኝ ዋጋዬ ይህ ነው” ያለችውን ወይንዋንና በለስዋን አጠፋለሁ፤ ዱርም አደርገዋለሁ፥ የምድረ በዳም አራዊት ይበሉታል። 15 በበኣሊም የበዓል ቀኖች ዕጣን ለእነርሱ በማጠንዋና ራስዋን በጉትቾችዋና በጌጥዋ በማስጌጥ ውሽሞችዋን ተከትላ እኔን በመርሳትዋ እቀጣታለሁ፥ ይላል ጌታ። 16 ስለዚህ፥ እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ። 17 ከዚያም የወይን ቦታዎችዋን፥ የተስፋ በርም እንዲሆናት የአኮርን ሸለቆ እሰጣታለሁ፤ በዚያም ከግብጽ ምድር እንደ ወጣችበት ቀን እንደ ብላቴንነትዋ ወራት ትዘምራለች። 18 “በዚያ ቀን፦ ‘ባሌ’ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ ዳግመኛ፦ ‘በኣሌ’ ብለሽ አትጠሪኝም፥ ይላል ጌታ፤ 19 የበኣሊምን ስም ከአፏ አስወግዳለሁና፥ ከእንግዲህም ወዲህ በስማቸው የሚያስታውሳቸው አይኖርም። 20 በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች በምድርም ላይ ከሚሳቡ ፍጥረቶች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ ቀስትንና ሰይፍን ጦርነትንም ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፤ በደኅንነትም እንዲያርፉ አደርጋቸዋለሁ። 21 ለዘለዓለምም ለእኔ እንድትሆኚ አጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍርድ፥ በምሕረትና በጽኑ ፍቅር ለእኔ አጭሻለሁ። 22 ለእኔም እንድትሆኚ በታማኝነት አጭሻለሁ፤ አንቺም ጌታን ታውቂአለሽ። 23 “እንዲህም ይሆናል፥ በዚያን ቀን እመልሳለሁ ይላል ጌታ፥ ለሰማይ እመልሳለሁ፥ ሰማይም ለምድር ይመልሳል፤ 24 ምድርም ለእህልና ለወይን ጠጅ ለዘይትም ትመልሳለች፤ እነርሱም ለኢይዝራኤል ይመልሳሉ። 25 በምድርም ላይ ለራሴ እንድትሆን እዘራታለሁ፤ ምሕረትም የሌላትን እምራለሁ፥ ሕዝቤም ያልሆነውን፦ ‘አንተ ሕዝቤ ነህ’ እለዋለሁ፤ እርሱም፦ ‘አንተ አምላኬ ነህ’ ይለኛል።” |