ሆሴዕ 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የእስራኤል ኃጢአት እና ምርኮ 1 እስራኤል ፍሬውን የሚሰጥ የተትረፈረፈ ወይን ነው፤ እንደ ፍሬው ብዛት መሠዊያዎችን አብዝቶአል፤ እንደ ምድሩም ብልጥግና መጠን ሐውልቶችን እያሳመሩ ሠርተዋል። 2 ልባቸው ሐሰተኛ ነው፤ በደላቸውን አሁን ይሸከማሉ፤ ጌታ መሠዊያዎቻቸውን ይሰባብራል፥ ሐውልቶቻቸውን ያጠፋል። 3 አሁንም፦ “ጌታን አልፈራንምና ንጉሥ የለንም፤ ንጉሥስ ለእኛ ምን ያደርግልናል?” ይላሉ። 4 የማይረባውን ቃላት ተናገሩ፤ በሐሰት መሐላ ቃል ኪዳን አደረጉ፤ ስለዚህ መርዛም አረም በእርሻ ትልሞች ላይ እንደሚበቅል መቅሠፍት በቀለባቸው። 5 የሰማርያ ሰዎች የቤትአዌንን እምቦሳ ፈሩ፤ ክብሩ ከእርሱ ተለይቶታልና ሕዝቡ ያለቅሱለታል፥ የጣዖቱ ካህናትም እሪ ብለው ይጮኹለታል። 6 እርሱም ደግሞ ለታላቁ ንጉሥ እጅ መንሻ እንዲሆን ወደ አሦር ተማርኮ ይወሰዳል፤ ኤፍሬምን እፍረት ይይዘዋል፥ እስራኤልም በምክሩ ያፍራል። 7 ሰማርያ ከንጉሥዋ ጋር በውኃ ላይ እንደሚሳፈፍ ስንጥር ትጠፋለች። 8 የእስራኤል ኃጢአት የሆኑት የአዌን የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፤ እሾኽና አሜከላ በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላል፤ እነርሱም ተራሮችን፦ “ሸፍኑን!” ኮረብቶችንም፦ “ውደቁብን!” ይሉአቸዋል። 9 እስራኤል ሆይ! ከጊብዓ ዘመን ጀምረህ ኃጢአትን ሠርተሃል፤ በዚያ ጸንተዋል፤ በዓመፀኛ ልጆች ላይ በጊብዓ ጦርነት አይደርስባቸውምን? 10 በፈቀድሁም ጊዜ እገሥጻቸዋለሁ፤ እጥፍ ስለ ሆነው በደላቸው በታሰሩ ጊዜ አሕዛብ በእነርሱ ላይ ይሰበሰቡባቸዋል። 11 ኤፍሬም ማበራየት የምትወድ የተገራች ጊደር ነበር፥ እኔም በውብ አንገትዋ ላይ አልጫንኩባትም፤ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፥ ይሁዳም ያርሳል፥ ያዕቆብም ለራሱ አፈሩን ያለሰልሳል። 12 ጌታ መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የመሻት ዘመን ነውና ጽድቅን ለራሳችሁ ዝሩ፥ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ሰብስቡ፥ ያልታረሰ መሬታችሁን እረሱ። 13 ክፋትን አርሳችኋል፥ ኃጢአትንም አጭዳችኋል፥ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፤ በኃያላንህ ብዛት፥ በመንገድህም ላይ ታምነሃልና። 14 በሕዝብህ መካከል ሽብር ይነሣል፤ ምሽጎችህም ሁሉ ይፈርሳሉ፤ ሰልማን ቤትአርብኤልን በጦርነት ቀን እንዳፈረሰ፥ እናትም ከልጆችዋ ጋር ተዳምጣ ነበር። 15 ቤቴል ሆይ! ከኃጢአታችሁም ክፋት የተነሣ እንዲሁ ይደረግባችኋል፤ ጎሕ ሲቀድ የእስራኤል ንጉሥ ፈጽሞ ይጠፋል። |