Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዕብራውያን 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት

1 እንግዲህ ከተናገርነው ነገር ዋናው ይህ ነው፦ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤

2 እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።

3 ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና፤ ስለዚህ ይህም ካህን የሚያቀርበው አንድ ነገር ሊኖረው ግድ ነው።

4 እንግዲህ በምድር ቢኖርስ፥ እንደ ሕግ መባን የሚያቀርቡት ስላሉ፥ ካህን እንኳ ባልሆነም፤

5 ሙሴ ድንኳኒቱን ሊሠራ በነበረ ጊዜ፥ “በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ፤” ብሎት ነበርና፤ እነርሱ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ።

6 አሁን ግን በተሻለ ተስፋ ቃል ስለ ተመሠረተ፥ መካከለኛ የሆነበት ኪዳን የተሻለ እንደሆነ ሁሉ፥ የተቀበለውም አገልግሎት ከእነርሱ አገልግሎት ይበልጣል፥፥

7 ፊተኛው ኪዳን ጉድለት ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር።

8 ጉድለት አግኝቶባቸዋልና እንዲህ ይላቸዋል፦ “እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምመሠርትበት ወራት ይመጣል፥ ይላል ጌታ፤

9 ከግብጽ ምድር ለማውጣት እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና እኔም ቸል አልኳቸው፤ ይላል ጌታ።

10 ከዚያ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው፥ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆንላቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑልኛል።

11 እያንዳንዱም ‘ጌታን እወቅ፥’ ብሎ ጐረቤቱን ወይም ወንድሙን አያስተምርም፤ ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና።

12 በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስብም።”

13 “አዲስ” በሚል ጊዜ ፊተኛውን አሮጌ አድርጎታል፤ ስለዚህ ጊዜው ያለፈበትና አሮጌው ነገር ሁሉ የሚጠፋበት ጊዜ ተቃርቧል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች