Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዕብራውያን 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ስለዚህ የክርስቶስን የመጀመሪያ ትምህርት አልፈን ወደ ፍጻሜ እንሂድ፤ መሠረትን ደግመን አንመሥርት፤ እርሱም ከሞተ ሥራ ንስሓና በእግዚአብሔር እምነት፥

2 ስለ ጥምቀቶችና እጆችንም ስለ መጫን ስለ ሙታንም ትንሣኤ ስለ ዘላለም ፍርድም ነው።

3 እግዚአብሔርም ቢፈቅድ ይህን እናደርጋለን።

4 እንደዚህ ያሉ ሰዎች ወደ ንስሓ መመለስ እንዴት ይቻላል!? አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸው፥ ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱ፥ ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩ፥

5 መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና መጪውንም የዓለም ኃይል የቀመሱ፥

6 ከዚህ ሁሉ በኋላ ቢክዱ፥ እነርሱ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ እንደገና ስለሚሰቅሉትና ስለሚያዋርዱት፥ አይቻልም።

7 ብዙ ጊዜ በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣ መሬት፥ ለሚያርሱአትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል፥ ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና፤

8 እሾህና ኩርንችትን ግን ብታወጣ፥ ጥቅም አይኖራትም፤ ለመረገምም ትቀርባለች፤ መጨረሻዋም መቃጠል ነው።

9 ስለ እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ! ምንም እንኳ እንዲህ ብንናገር፥ አብልጦ የሚሻለውና ለመዳን የሚሆነው እንደሚሆንላችሁ እርግጠኝነት ይሰማናል።

10 እግዚአብሔር፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዐመፀኛ አይደለምና።

11 እናንተም ሁላችሁ በተስፋ የምትጠባበቁትን ነገር እስክትጨብጡ ድረስ ትጋታችሁን እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን፤

12 ያም በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አይደለም።


የእግዚአብሔር ተስፋ እርግጠኛነት

13 እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ፥ የሚምልበት ከእርሱ የበለጠ ሌላ ማንም ስለ ሌለ በራሱ ማለ፤

14 እንዲህ ሲል፥ “በእውነት መባረክን እባርክሃለሁ፤ ማብዛትንም አበዛሃለሁ፤”

15 እንዲሁም እርሱ ከታገሰ በኋላ ተስፋውን አገኘ።

16 ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጠው ይምላሉ፤ ንግግራቸውንም በመሐላ በማጽናት የክርክር ሁሉ ፍጻሜ ይሆናል፤

17 ስለዚህም እግዚአብሔር የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደ ማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ፥ በመሓላ በመካከል ገባ፤

18 ይሄውም እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይቻል በሁለት በማይለወጥ ነገር፥ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት እንዲሆንልን ነው።

19 ይህም ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ አለን፤ እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ ነው፤

20 በዚያም እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው ኢየሱስ ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ ገባ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች