ዕብራውያን 5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኅጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤ 2 እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚሳሳቱት ሊራራላቸው ይችላል፤ 3 በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል። 4 እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ካልተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም። 5 እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም፤ ነገር ግን “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤” ያለው እርሱ ነው፤ 6 እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ “አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ” ይላል። 7 እርሱም ሥጋ ለብሶ በምድር በሚመላለስ ጊዜ፥ ከሞት ሊያድነው ወደሚችል፥ ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤ ስለ ጻድቅ ፍርሃቱም ጸሎቱ ተሰማለት፤ 8 ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ 9 ፍጹም ሆኖ ከተገኘም በኋላ ለሚታዘዙት ሁሉ ለዘለዓለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው። 10 በእግዚአብሔርም እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ተጠራ። ስለ ክህደት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ 11 ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፤ ለማድመጥ በድንዛዜ ላይ ስለ ሆናችሁ፥ ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው። 12 እስከ አሁን በነበረው ጊዜ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ እንደገና የእግዚአብሔር ቃላት የመጀመሪያውን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ ሰው ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። 13 ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅም፤ 14 ጠንካራ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ግን መልካሙንና ክፉውን የመለየት ልምድ ያላቸው ብስለት ያላቸው ሰዎች ናቸው። |