ዘፍጥረት 25 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የኬጡራ ዘሮች 1 አብርሃም ኬጡራ የምትባል ሌላ ሚስት አገባ። 2 እርሷም ዚምራንን፥ ዮቅሻንን፥ ሜዳንን፥ ምድያምን፥ የሽቦቅን፥ እና ሹሐን ወለደችለት። 3 ዮቅሻንም ሳባንና ድዳንን ወለደ። የድዳንም ልጆች አሹራውያን፥ ለጡሻውያንና፥ ለኡማውያን ናቸው። 4 የምድያምም ልጆች ዔፋ፥ ዔፈር፥ ሐኖክ፥ አቢዳዕና ኤልዳዓ ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው። 5 አብርሃምም የነበረውን ሁሉ ለይስሐቅ ሰጠው፥ 6 ነገር ግን የአብርሃም ለነበሩትም ለቁባቶቹ ልጆች አብርሃም ስጦታ ሰጣቸው፥ እርሱም ገና በሕይወቱ ሳለ ከልጁ ከይስሐቅ ለይቶ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደ ምሥራቅ አገር ሰደዳቸው። የአብርሃም መሞት 7 አብርሃምም በሕይወት የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሰባ አምስት ዓመታት ናቸው። 8 በመጨረሻዋ እስትንፋሱ አብርሃም ነፍሱን ሰጠ፥ በመልካምም ሽምግልና ሞተ፥ ሸምግሎ፥ ብዙ ዘመንም ጠገበ፥ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። 9 ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤል፥ ከመምሬ በስተ ምሥራቅ በሒታዊው በጾሐር ልጅ በዔፍሮን እርሻ ውስጥ፥ ማክፌላ በተባለ ዋሻ ቀበሩት። 10 የእርሻው ቦታ አብርሃም ከሒታውያን ላይ የገዛው ነው፤ ከዚያም አብርሃም ከሚስቱ ሣራ ጋር ተቀበረ። 11 ከአብርሃም ሞት በኋላም እግዚአብሔር ልጁን ይስሐቅን ባረከው፤ ይስሐቅም ብኤር-ላሃይ-ሮኢ ተብሎ በሚጠራው ምንጭ አጠገብ ኖረ። የእስማኤል ዘሮች 12 የሣራ አገልጋይ ግብጻዊትዋ አጋር ለአብርሃም የወለደችው የአብርሃም ልጅ የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው፤ 13 በትውልዳቸው ቅደም ተከተል የተዘረዘሩት የእስማኤል የልጆቹ ስም እንዲህ ነው፥ የእስማኤል የበኩር ልጁ ነባዮት፥ እና ቄዳር፥ አድብኤል፥ ሚብሣም፥ 14 ሚሽማዕ፥ ዱማ፥ ማሣ፥ 15 ሐዳድ፥ ቴማ፥ ይጡር፥ ናፊሽ እና ቄድማ ናቸው። 16 የእስማኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ስማቸውም በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው ይኸው ነው፥ በየወገናቸውም ዐሥራ ሁለት አለቆች ናቸው። 17 እስማኤልም የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው፥ የመጨረሻዋ እስትንፋሱን ተንፍሶም ሞተ፥ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። 18 ዘሮቹም ከግብጽ በስተ ምሥራቅ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ በሐዊላና በሹር መካከል ሲሰፍሩ፤ የኖረውም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት በተቃርኖ ነበር። የዔሳውና የያዕቆብ መወለድ 19 የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድም ይህ ነው፥ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፥ 20 ይስሐቅም አርባ ዓመት ሲሆነው ርብቃን አገባ፥ እርሷም በመስጴጦምያ የሚኖሩ የሶርያዊው የባቱኤል ልጅና የሶርያዊው የላባ እኅት ናት። 21 ርብቃ መኻን ስለ ነበረች ይስሐቅ ስለ እርሷ ወደ ጌታ ጸለየ፤ ጌታም ጸሎቱን ስለ ሰማ ርብቃ ፀነሰች፤ 22 ልጆቹም በማሕፀንዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤ እርሷም፥ “እንዲህ እሆን ዘንድ ከሆነ፥ ስለምንድን ነው የምኖረው?” አለች። ከጌታም ምላሽ ታገኝ ዘንድ ሄደች። 23 ጌታም እንዲህ አላት፥ “ሁለት ሕዝቦች በማሕፀንሽ አሉ፤ ሁለቱም ወገኖች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤ አንዱም ከሌላው ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል።” 24 የመውለጃዋም ሰዓት በደረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ በማኅፀንዋ መንታ ነበሩ። 25 በመጀመሪያም የወጣው ቀይ ነበረ፥ ሁለንተናውም ጠጉር ለብሶ ነበር፥ ስለዚህ ዔሳው ብለው ጠሩት። 26 ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ፥ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ያዕቆብ ተባለ። ልጆቹን በወለደች ጊዜ ይስሐቅ ሥልሳ ዓመት ሆኖት ነበር። 27 ልጆቹም ባደጉ ጊዜ፥ ዔሳውም በዱር የሚውል ብልኅ አዳኝ ሆነ፥ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፥ በቤትም ይቀመጥ ነበር። 28 ይስሐቅም ዔሳው ካደነው ይበላ ነበርና ይወደው ነበር፥ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበር። 29 ከዕለታት አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ ሲሠራ፥ ዔሳው ከአደን መጣ፤ በጣም እርቦት ነበር፤ 30 ዔሳውም ያዕቆብን፥ “ከዚህ ከቀዩ ወጥ አብላኝ፥ እኔ እጅግ እርቦኛልና!” አለው፤ (ኤዶም የተባለውም በዚህ ምክንያት ነበር።) 31 ያዕቆብም፥ “በመጀመሪያ ብኩርናህን ሽጥልኝ” አለው። 32 ዔሳውም “እኔ መሞቴ ነው፤ ታዲያ ብኲርና ምን ያደርግልኛል?” አለው። 33 ያዕቆብም፥ “እስኪ በቅድሚያ ማልልኝ” አለው። ስለዚህ ዔሳው ምሎ ብኲርናውን ለያዕቆብ ሸጠ። 34 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ ዔሳውም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ፤ በዚህ ዓይነት ዔሳው ብኩርናውን አቃለላት። |