ገላትያ 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የባልንጀራን ሸክም ስለ መሸከም 1 ወንድሞች ሆይ! ሰው ማንኛውንም ኃጢአት አድርጎ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ዓይነቱን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተም እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። 2 የእርስ በርሳችሁን ሸክም ተሸከሙ፥ በዚህም የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ። 3 አንድ ሰው ምንም ሳይሆን አንድ ነገር የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። 4 እያንዳንዱ የገዛ ሥራውን ይፈትን፤ ከዚያም በኋላ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፥ ስለ ሌላው ግን አይደለም። 5 እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ይሸከማልና። 6 ቃሉን የሚማር መልካሙን ነገር ሁሉ ከሚያስተምረው ጋር ይካፈል። 7 አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፤ ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳልና። 8 ምክንያቱም ወደ ገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፥ በመንፈስ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘለዓለምን ሕይወት ያጭዳል። 9 መልካምን ሥራ ለመሥራት አንታክት፥ ካልዛልን ወቅቱ በደረሰ ጊዜ እናጭዳለንና። 10 ስለዚህ ጊዜ ሳለን ለሰው ሁሉ፥ በተለይም ለእምነት ቤተሰቦች መልካም እናድርግ። የመጨረሻ ምክርና ሰላምታ 11 እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ። 12 በሥጋ መልካም ሆነው መታየት የሚፈልጉ ሁሉ እንድትገረዙ አስገደዱአችሁ፤ ይህን ያደረጉት ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው። 13 የተገረዙት ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም፥ ነገር ግን በሥጋችሁ እንዲመኩ እንድትገረዙ ይፈልጋሉ። 14 ለእኔ ግን፥ ዓለም ለእኔ እኔም ለዓለም ከተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት አይሁንብኝ። 15 አዲስ ፍጥረት መሆን እንጂ፥ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። 16 በዚህ ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ እና በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። 17 እኔ የኢየሱስን ምልክት በሰውነቴ ላይ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ። 18 ወንድሞች ሆይ! የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን። |