ገላትያ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ጳውሎስን ሐዋርያት እንደ ተቀበሉት 1 ከዚያ ከዐሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፥ ቲቶንም ከእኔ ጋር ይዤው ሄድሁ፤ 2 እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም ሮጬ እንዳልሆን፥ በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል፥ በመሪነታቸው ለታወቁት ለብቻቸው አስታወቅኋቸው። 3 ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረው ቲቶ እንኳ፥ ግሪካዊ ቢሆንም እንዲገረዝ አልተገደደም፤ 4 ይህም ወደ ባርነት ሊመልሱን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን ነጻነታችንን ሊሰልሉ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ። 5 የወንጌሉ እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ አልተገዛንላቸውም። 6 መሪዎች መስለው የሚታዩት፥ በፊት ምን እንደ ነበሩ ለእኔ ለውጥ የለውም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ መሪዎች የሚመስሉት ምንም ነገር አልጨመሩልኝም፤ 7 በአንጻሩ ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት እንደተሰጠው፥ እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደተሰጠኝ አዩ፤ 8 ጴጥሮስን ለተገረዙት ሐዋርያ እንዳደረገው፥ እኔንም ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ አድርጎኛል። 9 የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ ምሰሶዎች መስለው የሚታዩ ያዕቆብ፥ ኬፋና ዮሐንስ፥ እነርሱ ወደ ተገረዙት እኛ ወደ አሕዛብ እንድንሄድ ለእኔና ለበርናባስ የኅብረት ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ 10 ድሆችን እንድናስብ ብቻ ለመኑን፤ እኔም ይህን ለማድረግ እተጋበት የነበረ ነው። ጳውሎስ በአንጾኪያ ጴጥሮስን እንደ ተቃወመው 11 ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ሊፈረድበት ይገባ ስለ ነበር ነው። 12 አንዳንድ ሰዎች ከያዕቆብ ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበር፤ እነሱ በመጡ ጊዜ ግን የተገረዙትን ፈርቶ ወደ ኋላ አፈገፈገ፥ ራሱንም ለየ። 13 የቀሩት አይሁድ ግብዝነቱን ተከተሉ፥ በርናባስ ስንኳ ሳይቀር በግብዝነታቸው ተሳበ። 14 ነገር ግን እነርሱ ከወንጌሉ እውነት ጋር በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ፥ በሁሉም ፊት ኬፋን እንዲህ አልሁት፦ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለ እንደ አይሁድ ሳይሆን እንደ አሕዛብ የምትኖር ከሆነ፥ አሕዛብ አይሁድ እንዲሆኑ ለምን ታስገድዳቸዋለህ?” አይሁድም ሆኑ አሕዛብ በእምነት እንደሚድኑ 15 እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን፤ ከኃጢአተኞች አሕዛብ አይደለንም፤ 16 ሆኖም ሰው የሚጸድቀው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ በሕግ ሥራ እንዳልሆነ አውቀን፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንድንጸድቅ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል። ሥጋ ሁሉ በሕግ ሥራ አይጸድቅም። 17 ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ፥ እኛ ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ብንገኝ፥ ታዲያ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነውን? በጭራሽ አይደለም። 18 ይህን ያፈረስኩትን እንደገና የማንጽ ከሆንሁ፥ እኔ ራሴ ሕግ ተላላፊ ነኝ። 19 ለእግዚአብሔር እንድኖር በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼአለሁ፤ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ። 20 ክርስቶስ በእኔ ይኖራል እንጂ ከእንግዲህ ወዲያ እኔ አልኖርም፤ አሁን በሥጋ የምኖረው በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ በማመን የምኖረው ነው። 21 የእግዚአብሔርን ጸጋ አልናቅሁም፤ ጽድቅ በሕግ በኩል የሚገኝ ከሆነ እንግዲያውስ ክርስቶስ የሞተው በከንቱ ነው ማለት ነዋ! |