ዕዝራ 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ከዕዝራ ጋር የተመለሱ የቤተሰብ መሪዎች 1 በንጉሡ በአርጤክስስ መንግሥት ከእኔ ጋር ከባቢሎን የወጡ የአባቶች አለቆች እነዚህ ናቸው ትውልዳቸውም ይህ ነው፤ 2 ከፊንሐስ ልጆች ጌርሶን፥ ከኢታማር ልጆች ዳንኤል፥ ከዳዊት ልጆች ሐጡሽ፥ 3 ከሽካንያ ልጆች፥ ከፓርዖሽ ልጆች ዘካርያስና፥ ከእርሱም ጋር መቶ ሃምሳ ወንዶች ተመዝግበው ነበር። 4 ከፓሐት ሞዓብ ልጆች የዝራሕያ ልጅ ኤልይሆዔናይ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ወንዶች፤ 5 ከሽካንያ ልጆች የያሐዚኤል ልጅ፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ወንዶች፤ 6 ከዓዲን ልጆች የዮናታን ልጅ ዔቤድ፥ ከእርሱም ጋር ሃምሳ ወንዶች። 7 ከዔላም ልጆች የዓታልያ ልጅ ይሻዕያ፥ ከእርሱም ጋር ሰባ ወንዶች፤ 8 ከሽፋጥያ ልጆች የሚካኤል ልጅ ዝባድያ፥ ከእርሱም ጋር ሰማንያ ወንዶች። 9 ከዮአብ ልጆች የይሒኤል ልጅ ዖባድያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ዐሥራ ስምንት ወንዶች፤ 10 ከሽሎሚት ልጆች የዮሲፍያ ልጅ፥ ከእርሱም ጋር አንድ መቶ ስድሳ ወንዶች። 11 ከቤባይ ልጆች የቤባይ ልጅ ዘካርያስ፥ ከእርሱም ጋር ሀያ ስምንት ወንዶች፤ 12 ከዓዝጋድ ልጆች የሃቃጣን ልጅ ዮሐናን፥ ከእርሱም ጋር አንድ መቶ ዐሥር ወንዶች። 13 ከአዶኒቃም ልጆች የመጨረሻዎቹ ስማቸው ይህ ነው፤ ኤሊፌሌጥ፥ ይዒኤልና ሽማዕያ፥ ከእነርሱም ጋር ስድሳ ወንዶች፤ 14 ከቢጉቫይ ልጆች ዑታይና ዛቡድ፥ ከእነርሱም ጋር ሰባ ወንዶች። የቤተ መቅደስ አገልጋዮች 15 ወደ አኅዋ በሚፈሰው ወንዝ ሰበሰብኋቸው፥ በዚያም ሦስት ቀን ሰፈርን፤ ሕዝቡንና ካህናቱን ስመለከት በዚያ ከሌዊ ልጆች ማንንም አላገኘሁም። 16 ወደ አለቆቹም ወደ ኤሊዔዘር፥ አሪኤል፥ ሽማዕያ፥ ኤልናታን፥ ያሪብ፥ ኤልናታን፥ ናታን፥ ዘካርያስ፥ ሜሹላምና እንዲሁም ወደ መምህራኑ ወደ ዮያሪብና ኤልናታን ላክሁ። 17 በካሲፍያ ስፍራ አለቃ ወደ ሆነው ወደ ኢዶ ላክኋቸው፥ ለአምላካችን ቤት አገልጋዮችን እንዲያመጡልን በካሲፍያ ስፍራ ለሚኖሩት ለኢዶና ለወንድሞቹ ለቤተ መቅደስ አገልጋዮች ምን የሚነግሩአቸውን አስታወቅኳቸው። 18 የአምላካችን መልካም እጅ በላያችን ላይ ስለ ነበረች፥ የእስራኤል ልጅ የሌዊ ልጅ ከሆነው ከማሕሊ ልጆች ወገን የነበረውን አስተዋይ ሰው ሼሬብያን፥ ከእርሱም ጋር ዐሥራ ስምንት ልጆቹንና ወንድሞቹን አመጡልን። 19 እንዲሁም ሐሻብያ ከእርሱም ጋር ከሜራሪ ልጆች ወገን የነበረውን ይሻዕያና ወንድሞቹንና ልጆቻቸው ሀያ ወንዶች። 20 ዳዊትና ባለሥልጣኖቹ ሌዋውያንን እንዲያገለግሉ ከመረጧቸው የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ውስጥ ሁለት መቶ ሀያ የቤተ መቅደስ አገልጋዮችን አመጡ፤ እነዚህም ሁሉ በየሥማቸው ተጠቅሰዋል። ጾምና ጸሎት 21 በአምላካችን ፊት ራሳችንን ዝቅ እንድናደርግ፥ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንድንለምን በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅሁ። 22 ንጉሡንም፦ “የአምላካችን እጅ በሚፈልጉት ሁሉ ላይ ለመልካም ነው፥ ኃይሉና ቁጣውም እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ነው” ብለን ተናግረን ነበርና በመንገድ ካለው ጠላት እንዲያድኑን ወታደሮችና ፈረሰኞች ከንጉሡ ለመጠየቅ አፍሬ ነበር። 23 ጾምን፥ አምላካችንን ስለዚህ ነገር ለመንን፤ እርሱም ልመናችንን ሰማ። ለቤተ መቅደስ የቀረበ ስጦታ 24 ከካህናቱ መሪዎች ዐሥራ ሁለት ሰዎችን፥ ሼሬብያን፥ ሐሻብያንና ከእነርሱም ጋር ዐሥር ወንድሞቻቸውን ለየሁ፤ 25 ንጉሡ፥ አማካሪዎቹ፥ ባለሥልጣናቱ በዚያም የተገኙት እስራኤል ሁሉ፤ ለአምላካችን ቤት የሰጡትን የብሩንና፥ የወርቁን፥ የዕቃውንም ስጦታ መዝኜ ሰጠኋቸው። 26 ስድስት መቶ ሃምሳ መክሊት ብር፥ አንድ መቶ መክሊት የብር ዕቃዎች፥ አንድ መቶ መክሊት ወርቅ፥ 27 አንድ ሺህ ዳሪክ የሚያወጡ ሀያ የወርቅ ሳሕኖች፥ ሁለት እንደ ወርቅ የከበሩ ከጥሩ ከሚያንጸበርቅ ናስ የተሠሩ ዕቃዎች መዝኜ በእጃቸው ሰጠኋቸው። 28 እኔም አልኋቸው፦ “እናንተ ለጌታ ተቀድሳችኋል፥ ዕቃዎቹም ቅዱስ ናቸው፤ ብሩና ወርቁም ለአባቶቻችን አምላክ ለጌታ በበጎ ፈቃድ የቀረበ መባ ነው፤ 29 በካህናት አለቆች፥ በሌዋውያን በእስራኤል አባቶች አለቆች ፊት በኢየሩሳሌም በጌታ ቤት ክፍሎች ውስጥ እስክትመዝኑ ድረስ በጥንቃቄ ጠብቋቸው።” 30 ካህናቱና ሌዋውያኑም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አምላካችን ቤት ለመውሰድ ብሩንና ወርቁን ዕቃዎቹንም በሚዛን ተቀበሉ። ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ 31 በመጀመሪያው ወር በዓሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ከአኅዋ ወንዝ ተነሣን። የአምላካችንም እጅ በላያችን ነበረ፥ እርሱም ከጠላት እጅና በመንገድ ላይም ከሚሸምቅ አዳነን። 32 ወደ ኢየሩሳሌም ደረስን፥ በዚያም ሦስት ቀን ቆየን። 33 በአራተኛውም ቀን ብሩ፥ ወርቁና ዕቃዎቹም በአምላካችን ቤት በካህኑ በኡሪያ ልጅ በምሬሞት እጅ ተመዘነ፤ ከእርሱም ጋር የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር ነበረ። ከእነርሱም ጋር ሌዋውያኑ የኢያሱ ልጅ ዮዛባድና የቢኑይ ልጅ ኖዓድያ ነበሩ። 34 በዚያን ሰዓት ሁሉም ነገር ተመዘነ፤ በሚዛንና በቍጥር ም ተመዘገበ። 35 ከእስር የመጡት ከምርኮ የተመለሱት ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት፥ ስለ እስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ ዘጠና ስድስት አውራ በጎች፥ ሰባ ሰባት ጠቦቶች፥ ለኃጢአት መሥዋዕት ዐሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። ይህ ሁሉ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ። 36 የንጉሡንም ትእዛዝ በወንዝ ማዶ ላሉት ለንጉሡ እንደራሴዎችና ገዢዎች ሰጡ፥ እነርሱም ሕዝቡንና የእግዚአብሔርን ቤት አገዙ። |